top of page

Eg'e/Clan

የድራሼ ሕዝብ የ “Eg’e” ወይም ጎሣ ሥርዓት አስተዳደር ያላቸው፣ ማህበረሰቡ እርስ በርስ የሚተዋወቅበት፣ የሚከባበርበት እንዲሁም የሚቀባበሉበት በዘጠኝ ጎሣ የተዋቀረ ሲሆን፤ ይህንን የጎሣ ሥርዓት አጀማመርን የሚገልጽ የተጻፈ ታሪክ ባይኖርም በአፈ ታሪክ ደረጃ ከዘጠኙ ጎሣዎች (ኬታያ፣ ካሪት፣ ካርጭት፣ ኤላይት፣ ካንስት፣ ማሊት፣ አርጋማይት፣ ኮላይት እና ካላይት) መካከል አራቱ ጎሣዎች (ኬታያ፣ ካሪት፣ ካርጭት እና ኤላይት) በስልቶያ ሆይባ ተራራ አካባቢ የሰፈሩ ፈሊሶች ናቸው ተብሎ ይታመናል:: በሌላ በኩል በታሪክ አጋጣሚ በሊበን ግዛት (በዛሬዋ ነገሌ) ድራሼ፣ ኮንሶ፣ ቡርጄ፣ ኦሮሞ (ቦረናን ጨምሮ) ከዘመነ መሐመድ ግራኝ በፊት አብሮ ይሮሩ እንደነበረ እና ያነም የተወሰኑ ጎሣዎች እንደነበሩአቸው ታሪክ ያስታውሳል:: እርስ በርስ በማታለል ምክንያት በተፈጠረው አለመግባባት ቡርጄ፣ ኮንሶና ድራሼ ሊበንን ለቅቀው ወደተለያየ ሥፍራዎች እንደፈለሱም በኋላም የተወሰኑ ጎሣዎች እንደተፈጠሩ ጻሐፍት ይናገራሉ::

ሌላው የ Eg’e/ጎሣ እሳቤ አንድ ጎሣ ከጥንት ከጠዋቱ ማህበረሰቡ በጣት በሚቆጠርበት ጊዜ ለእያንዳንዱ ወንድማማች የተለያየ የጎሣ ስም ተሰጥቶ ከዚያን ጊዜ ጀምሮ ከእያንዳንዱ የሚወለደው ያ ልጅ የአባቱን ጎሣ ስም እያገኘ የሚቀጥልበት የቤተሰብ ሐረጋዊ ሥርዓት ነው፡፡ በዚህ መሠረት አንድ ጎሣ ያላቸው ሰዎች ሁሉ በአንድ አካባቢም ይኑሩ፤ በኢትዮጵያ እንዲሁም በዓለም በየትኛውም ክፍልና ቦታ ያሉት ወንድምና እህት ናቸው ተብሎ ይታመናል፡፡ እርስ በርስ መጋባት ፈጽሞ ነውርና የተከለከለ ነው፡፡ አንድ ወንድ/ሴት ከጎሣው/ዋ ውጭ ካሉት ከስምንቱ ቀሪ ጎሣዎች ጋር መጋባት በባህሉ የተፈቀደ ነው፡፡ የወንዱ ጎሣ ብቻ ወደሚቀጥለው ትውልድ ሐረግ ሲተላለፍ የሴቷ ጎሣ በእርሷ ያበቃል፡፡ በአንድ ቤተሰብ የሚወለዱ ልጆች ሁሉ ያባታቸውን ጎሣ ስም ያገኛሉ፤ ያባታቸውም ጎሣ ይሆናሉ፡፡

በድራሼ ባህል እያንዳንዱ ሰው አንድ ጎሣ ስር ይተዳደራል፡፡ የሁለት ጎሣ ሰው መሆንም ይሁን ያለ ጎሣ መሆንም አይቻልም፡፡ ከሌላ አካባቢ የመጣ እንግዳ ሰው ቢኖር፤ ቀድሞ በጎሣ ሥርዓት ከሚተዳደሩ ማህበረሰብ የመጣ እንደሆነ መጀመሪያ በዚያ ማህበረሰብ ያገኘው ጎሣ ስም ተጠይቆ አንድ ዓይነት (The same clan) ስር እንዲተዳደር ይደረጋል፣ የጎሣ ሥርዓት ከሌለው ማህበረሰብ የመጣ ሰው ከሆነ ያስጠጋው ሰው ወደ አንድ ጎሣ መሪ ወስዶ ጎሣ ስም ይሰጠዋል፡፡ እነዚህ ሂደቶች ‘Dhalum’ literally s/he is born to the clan ወደተሰጠው ጎሣ መቀየር ወይም ልጅ የማድረግ ሥርዓት ነው፡፡ አዲሱ እንግዳ በገባበት ጎሣ ለሌላው የሚደረገው ጥበቃ፣ ጥቅም፣ እና ሌሎች ማህበራዊ መስተጋብር ሥርዓት ሁሉ ያገኛል ማለት ነው፡፡ በሕዝቡ ዘንድ የጎሣ ቁጥር መብዛትና ማነስ ምንም ዓይነት የተለየ እሳቤ የለውም፤ ሁሉም ጎሣ እኩል ነው፤ እኩል ዋጋ አለው፡፡

በድራሼ ሕዝብ ባህል እያንዳንዱ ጎሣ የሚመራበት ሥርዓት እና ጎሣ መሪዎች አሉአቸው፡፡ የጎሣ መሪ “Poldh” (plural = Poldhalla) ተብሎ የሚጠራ ሲሆን ትርጉሙ ጌታ/የበላይ አለቃ ማለት ነው፡፡ እንደ ሕዝቡ እምነት ‘Poldh’ (የጎሣ መሪ) ገና ሲወለድ የተለየ የተፈጥሮ ኃይል አብሮሆት (Supernatural Power Born with) ስለመሆናቸው መሪዎቹ የተለያየ ነገር ለምሳሌ ንብ፣ እህል፣ ጠጠር የመሳሰሉትን በእጃቸው ጨብጠው ይወለዳሉ የሚል ትርክት አላቸው፡፡ ይህንን ሀሳብ በሌላ ክፍል በሰፊው እናያለን፡፡ በአንድ ጎሣ ውስጥ ከአንድ በላይ የጎሣ መሪዎች ሊኖሩ ይችላሉ፡፡ ከዋናው የጎሣ መሪዎች በታች የመቃብር አለቆች (Poldh Possat) ሲኖሩ፤ እነርሱም ለተከታዮቻቸው የመቃብር ቦታ ያስተዳድራሉ፡፡


2 views0 comments

Recent Posts

See All

Geology and Geologic Resources of Ethiopia (Geol 502)

Course outline Chapter -1 African Geology Chapter-2 Geology and Structure of the Ethiopian Basement Chapter-3 Phanerozoic Sedimentation History of the Horn of Africa Chapter -4 Cenozoic Magmatism in t

Volcanology and Geothermal Resources (Geol 4132)

Course outline References Chapter -1 Application of Volcanological Observations to Geothermal Exploration Chapter-2 Recent Practical Advances in Volcanology Chapter-3 Pyroclastic Rocks as a Tool to Ev

Post: Blog2_Post
bottom of page