top of page

የዺራሼ ሕዝብ ታሪክ፤ ባህል እና የሚያምንባቸው ህልውናዎች

Updated: Apr 15, 2023

የዺራሼ ሕዝብ የሚያምንባቸው ህልውናዎች

· Dhirt (plural = Dhidha ‹‹ዺዻ››)

በዺራሼ ሕዝብ እሳቤ “Dhirt” ‹‹ዺርት›› የሚለው ቃል ወንድ የሚለውን ፆታን ከመግለጽ ባሻገር የማይበገር፣ ጀግና፣ ጠንካራ፣ የማይፈራ፣ ደፋር፣ ወዘተ የሚል የማህበረሰቡን ስነ ልቦናዊ ባህርይ የሚገልጽ ጠንከር ያለ መልዕክት አለው:: ተቃራኒው “Sagot” ሲሆን እሳቤው ቦቅቧቃ፣ ቡከን፣ የማይችል፣ ፈሪ፣ ወዘተ የሚሉትን ባህርይን ይገልጻል፡፡ ከዚህ የተነሣ ወንዱም ሆነ ሴቷ ለሥራ፣ ትግል፣ ጀግንነት፣ አይበገርነት ወዘተርፈ ሲነሣሡም ሆነ ሲሠሩ “sagot kodhem” ማለት ሣጎታ አይደለሁም ይላሉ:: በማህበረሰቡ ውስጥ sagot kodhem የሚለው እሳቤ የሕዝቡ ህልውና በወኔና ጀግንነት ላይ የተመሠረተ መሆኑን የሚገልጽ፤ ማንኛውንም ዓይነት ሁኔታና ግዳጅ በጀግንነት ሠርቼ እወጣዋለሁ እንጂ እጅ አልሰጥም ለማለት ነው፡፡ ከዚህ ከተላበሰው ወኔ፤ አስፈሪ ነገርን መከራንም ጨምሮ ለመጋፈጥና ለመቋቋም የሚያስችል የቆራጥነት ስሜት የተነሣ፣ ሕዝቡ “Dhirashaa” በሚል ስም ራሱን ይጠራል::

“Dhirashaa” የሚለው ስም “Dhirt” እና “Shaak” ከሚሉ ቃላት ጥምረት የመጣ ሲሆን dhirt የሚለው እሳቤ የማይበገር፣ ጀግና፣ ጠንካራ፣ ደፋር ወዘተ የሚል ትርጉም ሲኖረው shaak የሚለው ቃል እውነተኛ፣ እርግጥ፣ ሃቅ፣ ትክክለኛ ወዘተ ትርጉም አለው፡፡ ከሁለቱ ቃላት ጥምረት የተገኘው ፈሊሶች “Dhirashaa” ስም እውነተኛ ወንድ፣ ሃቀኛ ወንድ፣ ትክክለኛ ወንድ፣ ወዘተ የሚለውን ትርጉም ያለው ሲሆን፤ የግዕዝ ፊደላት የኩሽ ቋንቋ ቤተሰብ የሆነውን የ“Dhirashaa” ቋንቋ አነጋገር ስልትን በአግባቡ ስለማይገልጽ ለአሁኑ ድራሼ ተብሎ ቢጠራም፤ የቋንቋው ስነ ልሳን እያደገ ሲመጣ ወደ ፊት የቋንቋውን አነጋገር ስልትን (Pronounciation) ሊገልጸው በሚችለው በላቲን አጻጸፍ ዘዴ (Latin writing system) “Dhirashaa” ‹‹ዺራሼ›› ተብሎ በትክክል እንደሚጠራ ተስፋ እናደርጋለን::

· Eg’e/Clan

የዺራሼ ሕዝብ የ “Eg’e” ወይም ጎሣ ሥርዓት አስተዳደር ያላቸው፣ ማህበረሰቡ እርስ በርስ የሚተዋወቅበት፣ የሚከባበርበት እንዲሁም የሚቀባበሉበት በዘጠኝ ጎሣ የተዋቀረ ሲሆን፤ ይህንን የጎሣ ሥርዓት አጀማመርን የሚገልጽ የተጻፈ ታሪክ ባይኖርም በአፈ ታሪክ ደረጃ ከዘጠኙ ጎሣዎች (ኬታያ፣ ካሪት፣ ካርጭት፣ ኤላይት፣ ካንስት፣ ማሊት፣ አርጋማይት፣ ኮላይት እና ካላይት) መካከል አራቱ ጎሣዎች (ኬታያ፣ ካሪት፣ ካርጭት እና ኤላይት) በስልቶያ ሆይባ ተራራ አካባቢ የሰፈሩ ፈሊሶች ናቸው ተብሎ ይታመናል:: በሌላ በኩል በታሪክ አጋጣሚ በሊበን ግዛት (በዛሬዋ ነገሌ) ዺራሼ፣ ኮንሶ፣ ቡርጄ፣ ኦሮሞ (ቦረናን ጨምሮ) ከዘመነ መሐመድ ግራኝ በፊት አብሮ ይሮሩ እንደነበረ እና ያነም የተወሰኑ ጎሣዎች እንደነበሩአቸው ታሪክ ያስታውሳል:: እርስ በርስ በማታለል ምክንያት በተፈጠረው አለመግባባት ቡርጄ፣ ኮንሶና ድራሼ ሊበንን ለቅቀው ወደተለያየ ሥፍራዎች እንደፈለሱም በኋላም የተወሰኑ ጎሣዎች እንደተፈጠሩ ጻሐፍት ይናገራሉ::

ሌላው የ Eg’e/ጎሣ እሳቤ አንድ ጎሣ ከጥንት ከጠዋቱ ማህበረሰቡ በጣት በሚቆጠርበት ጊዜ ለእያንዳንዱ ወንድማማች የተለያየ የጎሣ ስም ተሰጥቶ ከዚያን ጊዜ ጀምሮ ከእያንዳንዱ የሚወለደው ያ ልጅ የአባቱን ጎሣ ስም እያገኘ የሚቀጥልበት የቤተሰብ ሐረጋዊ ሥርዓት ነው፡፡ በዚህ መሠረት አንድ ጎሣ ያላቸው ሰዎች ሁሉ በአንድ አካባቢም ይኑሩ፤ በኢትዮጵያ እንዲሁም በዓለም በየትኛውም ክፍልና ቦታ ያሉት ወንድምና እህት ናቸው ተብሎ ይታመናል፡፡ እርስ በርስ መጋባት ፈጽሞ ነውርና የተከለከለ ነው፡፡ አንድ ወንድ/ሴት ከጎሣው/ዋ ውጭ ካሉት ከስምንቱ ቀሪ ጎሣዎች ጋር መጋባት በባህሉ የተፈቀደ ነው፡፡ የወንዱ ጎሣ ብቻ ወደሚቀጥለው ትውልድ ሐረግ ሲተላለፍ የሴቷ ጎሣ በእርሷ ያበቃል፡፡ በአንድ ቤተሰብ የሚወለዱ ልጆች ሁሉ ያባታቸውን ጎሣ ስም ያገኛሉ፤ ያባታቸውም ጎሣ ይሆናሉ፡፡

በዺራሼ ባህል እያንዳንዱ ሰው አንድ ጎሣ ስር ይተዳደራል፡፡ የሁለት ጎሣ ሰው መሆንም ይሁን ያለ ጎሣ መሆንም አይቻልም፡፡ ከሌላ አካባቢ የመጣ እንግዳ ሰው ቢኖር፤ ቀድሞ በጎሣ ሥርዓት ከሚተዳደሩ ማህበረሰብ የመጣ እንደሆነ መጀመሪያ በዚያ ማህበረሰብ ያገኘው ጎሣ ስም ተጠይቆ አንድ ዓይነት (The same clan) ስር እንዲተዳደር ይደረጋል፣ የጎሣ ሥርዓት ከሌለው ማህበረሰብ የመጣ ሰው ከሆነ ያስጠጋው ሰው ወደ አንድ ጎሣ መሪ ወስዶ ጎሣ ስም ይሰጠዋል፡፡ እነዚህ ሂደቶች ‘Dhalum’ literally s/he is born to the clan ወደተሰጠው ጎሣ መቀየር ወይም ልጅ የማድረግ ሥርዓት ነው፡፡ አዲሱ እንግዳ በገባበት ጎሣ ለሌላው የሚደረገው ጥበቃ፣ ጥቅም፣ እና ሌሎች ማህበራዊ መስተጋብር ሥርዓት ሁሉ ያገኛል ማለት ነው፡፡ በሕዝቡ ዘንድ የጎሣ ቁጥር መብዛትና ማነስ ምንም ዓይነት የተለየ እሳቤ የለውም፤ ሁሉም ጎሣ እኩል ነው፤ እኩል ዋጋ አለው፡፡

በዺራሼ ሕዝብ ባህል እያንዳንዱ ጎሣ የሚመራበት ሥርዓት እና ጎሣ መሪዎች አሉአቸው፡፡ የጎሣ መሪ “Poldh” (plural = Poldhalla) ተብሎ የሚጠራ ሲሆን ትርጉሙ ጌታ/የበላይ አለቃ ማለት ነው፡፡ እንደ ሕዝቡ እምነት ‘Poldh’ (የጎሣ መሪ) ገና ሲወለድ የተለየ የተፈጥሮ ኃይል አብሮሆት (Supernatural Power Born with) ስለመሆናቸው መሪዎቹ የተለያየ ነገር ለምሳሌ ንብ፣ እህል፣ ጠጠር የመሳሰሉትን በእጃቸው ጨብጠው ይወለዳሉ የሚል ትርክት አላቸው፡፡ ይህንን ሀሳብ በሌላ ክፍል በሰፊው እናያለን፡፡ በአንድ ጎሣ ውስጥ ከአንድ በላይ የጎሣ መሪዎች ሊኖሩ ይችላሉ፡፡ ከዋናው የጎሣ መሪዎች በታች የመቃብር አለቆች (Poldh Possat) ሲኖሩ፤ እነርሱም ለተከታዮቻቸው የመቃብር ቦታ ያስተዳድራሉ፡፡

· ‘‘Ashkot’’/መሐላ

‘‘Ashkot’’ ወይም መሐላ የአንድ ነገር እውነትነት ማረጋገጫ ቃል ነው፡፡ የዺራሼ ማህበረሰብ እሴት የሆነው Ashkot/መሐላ የአንድን ነገር ስለመፈጸምም ሆነ ላለመፈጸም ማስረገጫ ነው፡፡ ስለሆነም ማህበረሰቡ በዋናነት በሦስት እሳቤ አካላት ይምላሉ፤ በእህት/ወንድም፣ በጎሣ እና በንጉሥ ስም፡፡ ወንዶች ‘Alawtawo’ ይላሉ (እህቴን እንደ ማለት ነው) ወይም የመጀመሪያ እህቱ ስም ጠርቶ ይምላሉ፤ ሴቶች ‘Alawawo’ ይላሉ (ወንድሜን እንደ ማለት ነው) ወይም የመጀመሪያ ወንድሙ ስም ጠርቶ ይምላሉ፡፡ ወንድም ወይም እህት የለላቸው ደግሞ ወላጆች በመጀመሪያ ልጃቸው ስም (አባት ሴት ልጁን፤ እናት ወንድ ልጇን)፣ ወንድ ልጅ ያባቱን እህት ስም (በአክስቱ) ሴት ልጅ ደግሞ በአባቷ ስም ይምላሉ፡፡ አንዳንድ ጊዜ ባልተለመደ ሁኔታ የመማያ ወንድም ወይም እህት እያለች (ከጥላቻ፣ ቅራኔ ምክንያት) ለልጃቸው ካላቸው ጥልቅ ፍቅር የተነሳ በልጃቸው ስም የሚምሉ አሉ፡፡ አሊያም ሁለቱም ፆታ በጎሣቸው ስም ይምላሉ፡፡ ለምሳሌ ጎሣቸው ‘Elayt’ የሆኑት ሰዎች ‘Elaya’ ይላሉ፡፡ በሦስተኛ ደረጃ የዺራሼ ማኅበረሰብ በጊዜው መሪ በሆነው ንጉሥ ስም ይምላል፡፡

በእንዲህ ዓይነት የዺራሼ ህብረተሰብ የአንድን ነገር እውነትነት ጥግ ለማስረገጥ በወንድሙ/እህቱ ስም ወይም በጎሣው ስም አሊያም በመጨረሻ ደረጃ የመሪው ንጉሡን ስም በመጥራት መሐላ ያደርጋል፡፡ ማህበረሰቡ ራሱን የሚያውቀው ጥቂት የሚናገር ቁጥብ፣ ጨዋ፣ ከውሸት የራቀ፣ የሰውን የማይነካ፣ ባህሉን የሚያከብር፣ ባጠቃላይ ‘Etant’ በሚባል እሴት ህልውና አብሮ ይኖራል፡፡ ከዚህ እሳቤ ተቃራኒ ያልተረጋገጠ መረጃ የሚያወሩ፣ ችኩል ችኩል የሚሉ፣ እውነት ላልሆነ ነገር የሚምሉ፣ ብዙ የሚናገሩ፣ የሰውን የሚፈልጉ፣ የባህል እሴትን አልፎ የሚታዩትን ‘Hawudha’ ብሎ ይጠራቸዋል፡፡

በዚህ መሠረት የአብዛኛው ማህበረሰብ ክፍል ‘Etant’ ሆኖ ጥቂት ክፍሉ ግን ‘Hawudha’ መሆኑን ህብረተሰቡ ስለሚያውቁት የማን መሐላ እውነት እንደሆነ ይታወቃል፡፡ በተደጋጋሚ የሚምሉትን ይገስጻቸዋል፤ ከአታላይነታቸው ተግባር እንዲመለሱ ይመክራቸዋል፡፡ የመሐላው እውነትነት በፍሬው ስለሚታወቅም የአብዛኛው መሐላ በማህበረሰብ ዘንድ ተቀባይነት ያለው ቢሆንም አሁን ላይ ይህ መልካም እሴት በአንዳንድ ሁኔታዎች በመሸረሸር ላይ ይገኛል፡፡

· ‘Man’ (Plural = ‘Manna’)//Hut//

የዺራሼ ማህበረሰብ ለመጠለያነት የሚገለገሉበት ቤት ‘man’/ጎጆ/ በመባል ይታወቃል፡፡ ማህበረሰቡ ‘man’/ጎጆ አሠራር መቼ፣ የትና እንዴት እንደጀመሩ በታሪክ ተሰንዶ የተቀመጠ ነገር ባይኖርም ለረጅም ዘመናት ጎጆ ቤትን ለመጠለያነትና ለተለያዩ አገልግሎት እንደሚጠቀሙ አፈ ታሪክ ያወሳል፡፡ እስከ ዛሬ ድረስም እየተጠቀሙበትም ይገኛሉ፡፡ ‘Man’/ጎጆ/ የሚለው ቃል በማህበረሰቡ ዘንድ ትርጉሙ፡-

1) ለሰው ልጅ መኖሪያነት የሚያገለግል ከእንጨትና ሳር ወይም መሰል የተሠራ ቤት

2) ለእንስሳት መጠለያነት (ፍዬል፣ ከብት፣ አህያ፣ ዶሮ፣ በግ፣ በቅሎ፣ ፈረስ፣)

3) እህልን፣ ወንጭፍን(‘Kallamma’)፣ ለመጠበቅ የሚሠራ ጎጆ

4) ትዳር፣ ኑሮ (መስ)

5) ሆዳም፣ በላተኛ

ጎጆ ቤት መጠንን፣ ዓላማን፣ ቦታንና ዓይነትን መሠረት በማድረግ ‘man gam’, ‘kot’/‘Honaa’, ‘Fat’, ‘kombba’, ‘Quula’, ‘Koha’ ተብሎ ይጠራል፡፡ እንጨት (ቀርከሀ፣ ሸንበቆ፣ ሌሎችም) እና ሳር ግብአት ሆነው ጎጆ ቤት በመሠረታዊነት የሚሠራው ‘Elit’ መሀል ላይ፣ ሳጋ ‘Qadh’ ወደ ‘Elit’ እየተሰገሰገ በማገር ‘Orot’ በአዙሪት እየተማገረ፣ እስከ መጨረሻው ቀጭኑ ማገር ‘Tart’ በየቆመ ቅል አንገት//upright funnel// ቅርጽ ይሠራል፡፡ በዚህ የተሠራው ሁሉም ጎጆ በሳር ‘Ayit’ ይከፈናል ‘Shuqa’፡፡ ሳሩ ሲከፈን ከመጨረሻው ማገር 30ሳሜ ተረፍ ብሎ ‘Tunfaa’ ሲነጠፍ፤ ሊጥ በ’Shuntot’ ቀዳዳ (ልክ ክር በመርፌ ቀዳዳ እንደሚያልፍ) አልፎ በግምት 20ሳሜ ርቀት እየተወጋ በሳጋ ላይ እየተሳበ ጎጆው የሚያምር ገፅታ እንዲኖረው በ’Shilanga’ ወደ ላይ እየተመታ፤ ቁንጮው ላይ ከሸክላ የተሠራ ጉልላት ‘Mashawat’/‘Haynatet’ ይጎለላል፡፡ ከ‘Mashawat’ በታች ከቀርከሃ የተሰራ ክፍት ቅርጫት በማስገባት ወይም ሸንበቆን በቅርጫት ቅርጽ አጠላልፎ እዛው የሚሠራው ‘Kentersa’ ወፎች ሸክላው ስር እንዳይኖር ይከለክላል፡፡ አንዳንድ ጊዜ ቤቶች ከአናት አንዳይበሰብሱ ከተለመደው /Out of normal/ ሳር ለበሳ ወጣ ያለ ቀርጽ /Karmacat/ ይሠራል፡፡

የጎጆው መጠን አነስ ያለ ከሆነ ተገድግዶ (በሰፋፊ ‘Hana’ ወይም በግድግዳ መሀል ‘Sumba’ ገብቶ በ ‘Karba’ ሦስት ቦታ ይታሰራል) ብቻ ይቆማል (ለምሳሌ Kombba፣ Quula፣ Koha)፤ መጠኑ ከመካከለኛ እስከ ትልቅ ከሆነ ግን ከአራት እስከ ዘጠኝ ወጋግራት/Qabaya/ በማቶት ወይም ዘንዶ /Marangaa/ ይደገፋል፡፡ ዋልታ ቤት ሆኖ ጣሪያው በአጥን የተደገፈ ጎጆ ቤቶች እምብዘም የተለመደ አይደልም፡፡ ድራሼ ሕዝብ የጎጆ ቤት በር መዝጊያነት የሚጠቀሙት ከቀርከሃ/ከሐረግ የተዘጋጀ ባህላዊ መዝጊያ /Karfa plural = Karfala/ ወይም /Toha/ ነው፡፡

‘Man gam’ የሚባለው ዋና ቤት ሆኖ አባትና እናት የሚተኙበት እንደ ሳሎን የሚያገለግል፤ አንዳንዴ እንስሳትም ሊታሰሩበት ይችላል፡፡ ሦስቱ ጉልቻ መሀል ቤት ተጎልቶ እራት ሲሠራ ብዙን ጊዜ ልጆች በዙሪያው ይጫወታሉ፡፡ ‘Kot’ የሚባለው ከጭስ ንክኪ የጸዳ፤ የክት አልባሳት የሚቀመጡበት፣ የክብር እንግዳ መቀበያ፣ ባብዛኛው ሴት ልጆች የሚያድሩበት ቤት ነው፡፡ ‘Fat’ (Plural = ‘Fatat’) ቤት የድራሼ ጎጆ ‘Man’ የተለየ ምናልባትም ዺራሼ ማህበረሰብ በታሪክ ከምድር ቤት በላይ አንድ ደረጃ በመጨመር ፎቅ ይጠቀሙ እንደ ነበር ያመላክታል፡፡ ‘Fat’ እንደማንኛውም ጎጆ ቤት ሆኖ በረጃጅም ወጋግራት ከፍ ብሎ ግድግዳውም በጣም ረዥም ነው፡፡ የግድግዳው ቁመት ዕኩል በሰፋፊ እንጨት ጥራቢ ‘Hana’/‘Pohola’ ርብራብ ‘Afittaa’ ይከፈላል፡፡ የምድር ቤቱና የአየር ቤቱ ከቋሚ ግድግዳ ውጭ የሚሸፈነው በቀርከሃ ፍልጥ /Kalet/ ጥልፍ ነው፡፡ ወደ አየር ቤት መውጫ ከእንጨት ተጠርቦ የሚዘጋጅ መወጣጫ /Fonfaayaa/ አለው፡፡ ‘kombba’ የሚባለው ጎጆ ቤት አነስተኛ ቤት ሆኖ የወጣት ወንዶች ወይንም ወጣት ሴቶች ማደሪያ እንዲሁም የጫጉላ ቤትም ነው፡፡ ‘Koha’ ጎጆ ቤቶች በጣም አነስተኛ ቤት ሆኖ የማሳ/እርሻ ላይ ቤት ነው፡፡ ‘Quula’ ያለ ወጋግር የሚሠራ አነስተኛ ቤት ሆኖ ከሌላው ለየት የሚያደርገው መቀለሻ ቦታው በዛፍ ላይ (በደና፣ ግራር፣ ሾላ፣ ወዘተ) ነው፡፡ ብዙ ጊዜ የማሳ ላይ ቤት ሲሆን አንዳንድ ጊዜ መኖሪያ ሠፈር ሊሠራ ይችላል፡፡ ዋና ዓላማው ከአንዳንድ አውሬ አደጋ ወይም ብንቢ ንድፈት ራስን ለመከላከል ነው፡፡

‘Pollot’‹‹ፖሎት››//የእህል ጉድጓድ// Pollot//Artifactual Hole//

የተመረጠ መሬትን በጀሶ፣ በድጅኖ፣ በደንጎራ አጥልቆ ቆፍሮ ጉድጓድን አድርጎ እህልን ነቀዝ እንዳይበላው መክተቻ ‘Pollot’‹‹ፖሎት››/የእህል ጉድጓድ/ ይባላል፡፡ የዺራሼ ሕዝብ ባህላዊ የእህል ጉድጓድ ወይም ‘Pollot’ ማእከል አንድ ጉድጓዶች /concentric holes/ በጥበባዊ አሠራር የተማሰ ነው፡፡ ከላይ ወደ ታች በአማካይ 33ሳሜ ራዲየስ የሚቆፈረው የመጀመሪያው ጉድጓድ ከ50-120ሳሜ ጥልቀት ይኖረዋል፡፡ በመጀመሪያው ጉድጓድ መሀል በአማካይ 23ሳሜ በየቆመ ማጥሊያ/ቅል አንገት//upright funnel// ቅርጽ ከ180-250ሳሜ የሚጠለቀው ሁለተኛውና ዋናው ጉድጓድ ይሆናል፡፡ በሁለተኛው ጉድጓድ ጫፍ ዙሪያ የሚቀረው 10ሳሜ ‘Matabet’ ሲባል፤ ለመርገጫነትና የዋናው ጉድጓድ መክደኛ ‘Palet’ እላዩ ላይ የሚያርፍበት ቦታ ነው፡፡ የጉድጓዱ መክደኛ /‘Palet’/ ጠፍጣፋ ክብ ድንጋይ ተጠርቦ /usually welded ignibrite/ አንዳንዴ በተፈጥሮ ጠፍጣፋ ክብ ድንጋይ ይሆናል፡፡

የጉድጓዱ ይዘት እንደየሰዉ አቅምና ዓላማ ሲለያይ፤ ባብዛኛው ከ7 እስከ 40 ኩንታል ይይዛል፡፡ ለጉድጓድ የሚመረጠው መሬት በዓይነት የተለየ ሲሆን፤ ብዙን ጊዜ የተጋገረ መሬት /baked land/ ባካባቢው ቦሮቦር ተብሎ የሚጠራ፣ የጠነከረ ሆፊ /consolidated pumice/ ባካባቢው ‘Ong’ ተብሎ የሚጠራ፣ በትንሹ የተፈረካከሰ ኮተቤ/ባርያ ድንጋይ፣ አልፎ አልፎ የጠነከረ ደለል /consolidated deposit/ ባካባቢው ‘Pusuqa’ ተብሎ የሚጠራ ሲሆን፤ ባጠቃላይ ውሃን እንዳይሰርግ የሚያስቀር መሬት ነው፡፡

ዋናው ጉድጓድ አፈር እንዳይገባበት መክደኛው ተከድኖበት ዙሪያው በጭቃ (አብዛኛውን ጊዜ የኩይሳ አፈር) ወይም የከብት እበት ይመረግና እላዩ ላይ የመጀመሪያ ደረጃ ጉድጓድ ከተመረጠው አፈር በደንብ በእግር ተረጋግጦ ከዙሪያው መሬት ጉብ እስኪል (ውሃ በቀላሉ እንዳይሰርግ ተብሎ) ድረስ ይለበሳል፡፡

የእህል ጉድጓድ እህልን በጥራት የማቆየት ሁኔታ እንደየአፈሩ ዓይነት እንዲሁም እህል ዓይነት የሚወሰን ሲሆን፤ ባብዛኛው ከዓመት እስከ 10 ዓመታት ያቆያል፡፡ የአፈሩ ተፅዕኖ እንዳለ ሆኖ እህል በጉድጓድ ውስጥ በቆየ ቁጥር ከጉድጓዱ ግድግዳ ወደ ውስጥ እየተጉዳ (inward damage) ይመጣል፡፡ ይህ የተጎዳው የእህል ክፍል ‘Kama’ ወይም ‘Kamamma’ ወይም ‘Qemaraa’ ይባላል፡፡

ሕብረተሰቡ ጉድጓድን እንደ የቁጠባ ባንክ ይጠቀመል፡፡ እህል ከጉድጓድ ውጭ በጎተራ ወይም በሌላ ስቀመጥ በቀላሉ ይባክናል የሚል እምነት አላቸው፡፡ አንድ ሰው አንድና ከዚያ በላይ ጉድጓዶች (እስከ አስር ድረስ) ሊኖሩት ይችላል፡፡ እንደየአፈሩ ሁኔታ፣ የጉድጓዱ ይዘትና ብዛት እንዲሁም የእህሉ ዓይነት የቱን በቅድሚያ የመጠቀም ቅደም ተከተል የሚወስን ቢሆንም ከአንድ ወር እስከ ሁለት ወራት ባለው ጊዜ አንድ ቤተሰብ ለመጠቀም የወሰኑትን ጉድጓድ ከፍቶ እህል በትንሽ በትንሹ ያወጣሉ፡፡ ሌላው የጉድጓድ እሳቤ እህልን ነቀዝ እንዳይበላው ማድረግ፣ ከሰው ሠራሽ አደጋ (እሳት፣ ዘረፋ) እና ከተፈጥሮ አደጋ (ጎርፍ) ወዘተ ለመከላከል ነው፡፡

እንግዲህ የእህል ጉድጓድ ጠቀሜታው ብዙ ቢሆንም አንዳንድ ጊዜ ለሌባ የመጋለጥ አዝማሚያ፣ ዝናብ በበዛበት ዓመት /’Par Toshat’/ ውሃ ሰርጎ የመግባት ችግር፣ እህል ጉድጓድ ውስጥ በቆየ ቁጥር የመበስበስ /’Kama’/ ዕድል፣ አልፎ አልፎ ከቆይታ የተነሳ ጉድጓድ ከነአካቶ የመጥፋት ሁኔታ፣ አንዳንድ አፈር (‘Pusuqa’) ነቀዝ ወይም በአካባቢው ‘Tummaysa’ ተብሎ በሚጠራው የመበላት አጋጣሚ እንዲሁም ሰው በስህተት/ስሁት የሌላ ሰውን ጉድጓድ ከፍቶ የመጠቀም አጋጣሚም ይኖራል፡፡

· Ayladhaa

‘Ayladhaa’ የሚለው ስም በዺራሼ ማህበረሰብ ዘንድ እጅግ የሚዘወተር ለመንፈስ ዓለም መጠሪያ የተሰጠ ስም ሲሆን፤ እሳቤውም ለሰው ልጅ መልካም ነገር ማድረግና መስጠት፣ በሌላ በኩል ደግሞ ሥርዓታቸውን ከተላለፍክ ጉዳትና ሞት በሰው እና ሀብቱ ላይ ማድረስ የሚችል የመላእክትም የሰይጣንም ባህርይ ያለው መንፈሳዊ ዓለም ነው ተብሎ ይታመናል፡፡

እንደ ማህበረሰቡ እምነት ‘Ayladhaa’ ወይም ‘‘መልአከ ሰይጣን’’ እንደ ሰው ልጅ የራሳቸው የሆነ ሥርዓትና ደንብ ያላቸው በራሳቸው ታዓምራዊ ዓለም የሚኖሩ፤ አልፎ አልፎ ለጥቂት ሰዎች በነጠላም ሆነ በቡድን ምትሐታዊ በሆነ መንገድ ሊታዩ የሚችሉ የመናፍስት ዓለም ናቸው፡፡ ‘Ayladhaa’ ይኖራሉ ተብሎ የሚታመነው የምንጭ ውሃ ወይም የከርሰ ምርድ ውሃ የዓለት ንቃቃትን ተከትሎ ውስን አካባቢን ያረጠበበት (water ooses up from very shallow water table) ሸለቋማ ስፍራ ነው፡፡ ማህበረሰቡ ያንን እርጥበት አዘል አካባቢን ተከትሎ የውሃ ጉድጓድ /Dug well/ ‘Eel’ (plural= ‘Eella’) ይቆፍራሉ፡፡ በዚህ እምነት ምክንያት ግን የጉድጓድ ውሃው ዙሪያ ሁሉ ይፈራል፤ ይከበራል፡፡ በዚህ መሠረት ቦታው አነስተኛ ደን ዙሪያውን ይከብባል፣ ወፍ፣ እባብ፣ ኤሊ፣ ዘንዶ፣ ማንኛውም ዓይነት ነፍሳት እንቁራሪትን ጨምሮ መንካት ማለትም መግደል እጅግ ነውር ነው፡፡ ደፍሮ የነካም ሰው እውነትም መንፈሳዊ ችግር ያጋጥመዋል፤ ሊሞትም ይችላል፡፡ በዚህ መሠረት በማህበረሰብ ላይ የሚሰራው የፍርሃት ድባብ እጅግ በጣም ከባድና ሰው ብቻውን በተለይም ቀትርና ሌሊት ወደ ስፍራዎቹ መሄድን አይደፍርም፡፡ ሌላው ቀርቶ ሰው በድንገት ተንሸራትቶ ቢወድቅ እንኳ አፈር ቀምሶ ሆነ ብሎ ይህንን የመውደቅ ድርጊት እንዳልፈጸመ ይገልጻል፡፡ ብዙውን ጊዜ አውሎ ንፋስ /‘Kota’/ መነሻውም ሆነ መድረሻው በዚሁ ምንጭ አካባቢ መሆኑ ከአንዳንድ እንደ እንቁራሪትና ወፎች ድምጽ በተለየ ሁኔታ ከመሰማቱ ጋር ተዳምሮ የፍርሃት ድባቡን በሰዎች አእምሮ ላይ ያከብዳል፡፡

ማህበረሰቡ የምንጭ ውሃዉን የዚህ የመንፈስ ዓለም የ‘Ayladhaa’ ሽንት ነው ብሎ ያምናል፡፡ ዝናብ በበዛበት ዓመት /’Par Toshat’/ ውሃዉ ጉድጓዱን ሞልቶ ሲፈስስ ‘Hetecen’e’ ይባላል ማለትም ሽንታቸው ተትረፈረፈ ለማለት ነው፡፡ ስለሆነም ውሃን ላለማጣት ለዚህ ‘‘መልአከ ሰይጣን’’ ክብር ይሰጣሉ፤ ለዚህ ሥራም ሰው ሰይሞ ከእነርሱ ጋር በመንፈስ ዓለም ያወራሉ፤ ችግር እንኳ ቢኖር በዚህ ሰውየዉ በኩል ይፈቱታል፡፡ ሰው በእነዚህ አካባቢ በተለይ ከመንደር ወጣ ወዳሉ ምንጮች/‘Iyga’ በድንገት እንደነ ኤሊ፣ ዘንዶ፣ እባብ፣ ወዘተ አይቶ ቢደነግጥ አሊያም ድንጋይ ወይም ሌላ ነገር ቢወረውርበት ‘Kaataa’/‘‘መንፈሳዊ ማንነቱ’’/ ይወሰድበታል የሚል እምነት ስላላቸው ያ ሰው ይታመማል፤ ሰላም ያጣል፤ ባጠቃላይ ተረብሾ ከሰውነት ተራ ወጥቶ ከሲታም ይሆናል፡፡ ከዚህ መናፍስት ዓለም ጋር የሚነጋገሩት ሰዎች የዚሁን ሰውየ ‘‘መንፈሳዊ ማንነት’’ /‘Kaataa’/ መቤዣ ከፍለው ካልተመለሰለት በስተቀር ጤንነቱ አይመለስም፡፡ ለዚህ መቤዣ ተብሎ የሚከፈለውን እንደነ ጨሌ፣ ክር፣ ባዘቶ፣ ወዘተ ምንጮች አካባቢ ማየት የተለመደ ነው፡፡

ታዲያ ማህበረሰቡ በእንደዚህ መልክ እምነት ይሁረው እንጂ መልአከ ሰይጣን ባህርይ ያለ ፍጥረት ስጀመር የለም፡፡ የፍጥረት ዓለም መልአክ አሊያም ሰይጣን ወገን በተቃራኒ ጫፍ እንዳለ ያስረዳል እንጂ በእሳቤም ሆነ በድርጊት መካከለኛ የሆነ ፍትረት ስለመኖሩ ፍጹም ፍንጭ አይሰጥም፡፡ በሌላ በኩል ደግሞ ከርሰ ምድር ውሃ ስንጥቃትንና ዝንፈትን/Fault/ ተከትሎ ወደ ውጭ ያዣል አሊያም ይፈስሳል እንጂ የዚሁ የመልአከ ሰይጣን ሽንት የሚባል ነገር በፍጹም የለም፡፡ ምናልባት የማህበረሰቡን ሥነ ልቦናዊ እምነትን ተከትሎ ሰይጣን ባህሪውን ቀይሮ ለመክበር በዚህ መልክ በውሃና ምንጮች አካባቢ ይገለጥላቸው እንጂ አንዴ ጥሩ ነገር የሚያደርግ ሌላ ጊዜ ደግሞ የሚገድል የፍጥረት ዓለም የለም፡፡ ‘Kaataa’ ወይም ‘መንፈሳዊ ማንነት’ የሚለው እሳቤም ከዚሁ የተለየ አይደለም፡፡ ሰው የሚወሰድበት መንፈሳዊ ማንነት የለውም፡፡ ነገር ግን ሰው ባመነበት እምነት ልክ ሊገለጥ የሚችል ፍጥረት ስለሆነ ማህበረሰቡ በሚያምኑት እሳቤ ልክ የሚፈጸምባቸው የመንፈስ አሠራር ሊኖር ይችላል፡፡ በ1960ዎቹ ወደ አካባቢው የደረሰውና እየተስፋፋ ያለው የወንጌል ትምህርት የዚህን የከሰረ አሰራር ድባቅ መቶ አሁን ሰው በነጻነት የትም መቼም መንቀሳቀስ፣ ውሃን መጠቀም መቻሉ የዚህ እምነት መሠረተ ቢስ ስለመሆኑ ጥሩ ማሳያ ነው፡፡ ይሁንና አሁንም የተወሰኑ ሰዎች ከቀድሞ ባህላዊ እምነት መላቀቅ ካለመቻላቸው የተነሳ እልፎ አልፎ የዚሁ ስውር ምስጢር አሰራር ሰለባ ሲሆኑ ይስተዋላሉ ያሳዝንማል፡፡

· ‘Ayma’//ፎራ//Abarn//

‘Ayma’ ወይም ፎራ ከመኖሪያ ሰፈር በኪሎ ሜትሮች ራቅ ብሎ በዋናነት የቀንድ ከብት በረት እንዲሀም አልፎ አልፎ ፍየል ጉረኖ መኖሪያ ቤት ነው፡፡ በዺራሼ ማህበረሰብ ባህል ከብት ከማህበረሰብ መኖሪያ ተለይቶ ወጣ ብሎ መሰማራትና መስፈር ለእንስሳቱ ነጻነት፣ ጤንነት፣ ባጠቃላይ ሁለንተናዊ እንቅስቃሴ መልካም ነው ተብሎ ይታመናል፡፡ ለእንስሳት መኖሪያነት ወሳኝ ሊሆን የሚችለው ጉብታና በቀላሉ የማይጨቀይ ቦታ ተመርጦ ጎጆ ቤት ‘Mana’ ለእረኛ፣ ፎራ መሪ እና ለሌሎች ተጠቃሚ ተሠርቶ፤ የከብት በረት/ጉረኖ በጠንካራ አጥር ይታጠራል፡፡ እንዲሁም ለጥጆች ለብቻ አነስተኛ በረት ይሠራል፡፡

‘Ayma’ ወይም ፎራ የሚመሠረተው በተወሰኑ የከብት/ፍየል ባለቤቶች ሲሆን እያንዳንዱ አባወራ በፎራው መተዳደሪያ ደንብ ይመራል፡፡ አባላቱ (ከአስር እስከ ሰላሳ የሚሆኑ) ከራሳቸው የፎራ አስተዳዳሪዎች (ዋና አስተዳዳሪ/Kadhayt wanna/፣ ምክትል አስተዳዳሪ/Kadhayt lakiya/ እና ገንዘብ ያዥ/Kadhayt pirret qabiyu/) ይሰይማሉ፣ የፎራ መሪ/Kadhayt Aymat/ (ከማህበረሰቡ አዋቂ፣ ጠንቃቃና በሳል ሽማግሌ ፈልጎ) ይሾማሉ፡፡ እንደ ፎራው ከብት ብዛት ሁለት የፎራ መሪዎች/Kadhaya Aymat ሊኖረው ይችላል፡፡

አስተዳዳሪዎቹ አጠቃላይ የፎራውን እንቅስቃሴ መቆጠጠር፣ መከታተል እንዲሁም ችግሮች ሲፈጠሩ የመፍትሔ ሁኔታ ማመቻቸት ነው፡፡ የፎራ መሪ ደግሞ የሚኖረው በፎራ ውስጥ ሆኖ የፎራውን የዕለት ተለት እንቅስቃሴ በቅርበት መከታተል ስለሆነ ሁሉንም ከብት በመልክ፣ በቁመት እንዲሁም የማን እንደሆነ ያውቃል፡፡ የአባላቱ የማሰማሪያ ቅደመ ተከተል በህሊናው መዝግቦ አንደኛው ተራውን ጠብቆ ሲጨርስ ለቀጣይ ተረካቢ መልዕክት መላክ/Dhammanta dham/፤ እበት ማስወገድ/መዛቅ፣ የከብቶቹን ደህንነት መከታተል፣ ችግር ካለ ለባለቤቱ ማሳወቅ፣ የወተት ቅልን ማጠን፣ የሚታለቡ ላሞችን የማን እንደሆኑ መለየት፣ ማለብ፣ ጥጃቸውን ማሰርና መልቀቅ፣ ወተታቸውን በየባለቤቱ የወተት ቅል ማጠራቀም፣ መናጥ፣ ቅቤውን ለባለቤቱ መላክ፣ እንዲሁም ጥጆች በተራ እንዲሰማሩ ማድረግ ይሆናል፡፡ ሁሉም አባላት ተረ በተራ አንዱ ከአንዱ ኋላ (በዛ ያለ መንጋ ከሆነ ሁለት ሆኖ ሊያግዱ ይችላሉ) ለሦስት ቀናት ከብቱን ያሰማራል፤ ይጠብቃልም፡፡ አንድ ከብት ያለውም ሆነ ስድሳ ከብቶች ያለው እኩል ሦስት ቀናት የመጠበቅ ግዴታና ኃላፊነት አለበት፡፡

ፎራዉ በቅርብ ርቀት ዙሪያውን ለሚያርሰው አርሶ አደር ማደሪያ ስፍራ ሆኖም ያገለግላል፡፡ ሁልጊዜ ለፎራ መሪ የማሽላ ዱቄት (በተለምዶ የ‘Rar’, ‘Kanshra’ ‘Kambubuuthaa’/በቆሎ) እና የሚጠጣ ‘Parshoot’ ‘Qala/Qalala’ ከተረኛው አባወራ የሚመጡለት ስንቆች ሲሆን ፎራ ለማደር የሚመጡ አርሶ አደር እሸት (በቆሎ፣ ‘Rar’፣ አዴንጓሬ)፣ ሚጥሚጣ፣ ‘Halokot’(ለጎመንነት የሚጠቅም የማህበረሰቡ ዋና ዛፍ ነው ወይም Moringa) እንዲሁም ይዞ ከወረደው ስንቅ ‘Parshoot’ ‘Qala/Qalala’ ሊይዙ ይችላሉ፡፡ ያመጡትን በጋራ ምግብ ቀቅሎ እንደተዘረገፈ እጅግ በትኩሱና ተንኮል በበዛበት የሚበላው ምግብ ‘Angara Dhama Imat’ ባገኙት ወተትና ‘Parshoot’/‘Qala በሽሚያ ይበላሉ፡፡ አንዳንዴ በዛ ያለ ሚጥሚጣ ወይም በርበሬ ጨለማን ተገን በማድረግ በሰው ፊት ያስቀምጡና ምግቡን ሲሻሙ የወሰደው ሰው በዚያ በርበሬ ሲለበለብ ለመሳቂያነት ያፌዙበታል፡፡

‘Ayma’ ወይም ፎራ ከሠፈር ርቆ በጫካ መከበቡ ሌሊት አልፎ አልፎ ከብቶቹን የሚተናኮሉ የዱር አራዊት እንደ አንበሳ፣ አቦ ሸማኔ፣ አኔር፣ ጅብ የመሳሰሉት ይመጣሉ፡፡ ለእንደዚህ ዓይነት አደጋ ቢመጣስ ተብሎ ጫፉ የእሳት ፍም ውስጥ ተከትቶ ያደረ የ‘Raphasaya’ እርጥብ ግንዶች ይኖራሉ፡፡ በአራዊቱ መራወጥ ከእንቅልፉ የነቃው ፎራ የተኛው ወጣትና አርሶ አደሩ ከተኛበት ብድግ ብሎ ጩኸቱን ለቅቆ፤ ከእሳት ግንዱን መዝዞ አየር ላይ ሲወረውር እርጥብ ‘Raphasaya’ በተፈጥሮ እሳታቸው አየር ላይ ስለሚፈነጣጠር አራዊቱ እግረ አውጭኝ ብሎ ሮጦ ይጠፋሉ፡፡ አንዳንዴ ግን የዱር አውሬው በተለይ አንበሳ ሾልኮ ወደ በረት ዘልሎ ገብቶ ከብት አንስቶ ከአጥር በላይ ወርውሮ ይበላል፡፡

· ‘Lollat’/መለከት

‘Lollat’/‹‹ሎላት››/ ከጥታዊት ኢትዮጵያ በጋርዱላ አካባቢ የሚገኘው የዺራሼ ማሕበረሰብ ለየት ባሉት ባህላዊ የሙዝቃ መሣሪያቹና ጨዋታዎቹ የታዋቀ ነው፡፡ የሙዝቃ መሣሪያዎቹ የትንፋሽ፣ የምት እና የክር ተብሎ በሦስት ይከፈላሉ፡፡ ከሰባቱ (Filla, Mayra, Tarba, Lollat, Kulluutot, Fitinfitayat, Fiilet) የትንፋሽ መሣሪያዎች አንዱ ‘Lollat’ ሲሆን፤ ባብዛኛው የጨዋታ ማድመቂያ መሣሪያ ነው፡፡

‘Lollat’ ‹‹ሎላት›› በአብዛኛው ከአጋም የሚሰራ ሲሆን፤ አንዳንዴ ከ‘Paatana’ እንጨት እና ከቀጫጭን ቀንድ በተለያየ መጠን ይሰራል፡፡ ‹‹ሎላት›› ቁመቱ ከ20ሣሜ እስከ 40ሣሜ የሚረዝም ሲሆን፤ ውፍረቱም እንደ ቁመቱ መጠን ይለያል፡፡ አሰራሩም የዱላ ያህል ውፍረት ያለው አጋም ወይም ‘Paatana’ ተቆርጦ ለቀናት ከጠወለገ በኋላ አንካሴ ወይም መሰል ብረት እሳት ውስጥ እያጋሉ ካንደኛው ጫፍ እያዞሩ ቀዳዳ ይበጃል፡፡ ቀዳዳው ጠልቆ ወደ መጨረሻዎቹ ሲደርስ (ጥልቀቱ በሳር ይለካል)፤ በተቃራኒው ጫፍ በወስፌ ይበሳል፡፡ በመጥረቢያ ከላይ ወደ ታች ውፍረቱን እያቀጠኑ ይጠረብና ቂጡ ጋር ተከርክሮ እንደገና በሹል ቅርጽ ይቀረጻል፡፡ እንዳትሰነጣጠቅ ቅቤ ወይም ሞራ ተሞልቶበት ለሳምንታት ተሰቅሎ ይቆያል፡፡ ውጭው ክፍል የበሬ ቆዳ ይሰፋበታል ወይም በ‘Losset’/esophagus ይለበጣል፡፡ አልፎ አልፎ ድምጹ ለዛ ሲያጣው ቅቤ እየተሞላበት ለማህበራዊ ግልጋሎት ይጠቀማሉ፡፡

‘Lollat’ ከማህበረሰቡ የሙዝቃ መሣሪያዎች ሁሉ ይልቅ በስፋት ጥቅም ላይ የሚውልና ከዕለት ተዕለት እንቅስቃሴ በተለይም ከእርሻ ሥራ ጋር ተያያዥነት ያለውና እያንዳንዱ ከተጠቃሚው መንደር የሚገኘው የ‹‹ሎላት›› ድምፅ በትክክል መለየት ይችላል፡፡ ምንጊዜም ንጋት ላይ ‹‹ሎላት›› ሦስት ዙር ሲነፋ፤ የመጀመሪያው መልዕክት ንቃ፣ ተዘጋጅ እና ተነሣ ማለትን ሲገልጥ፤ ይህ ለእርሻ ሥራዎቸ፣ ለአደን እና ለሌሎች ማህበራዊ እንቅስቃሴዎች መልእክት ማስተላለፊያ መንገድ ነው፡፡ መንገድ ከወጡ በኋላም ኋላ ለቀሩት ‹‹ሎላት›› ነፊው እየነፋ ያሉበትን ቦታ ያሳውቃል፡፡ ወደ ቤት ሲመለሱም እየተመለሱ መሆናቸውን ከሩቅ ‹‹ሎላት›› እየተነፋ ምናልባትም ከፊታቸው ዝግጅት መደረግ የሚያስፈልግ ከሆነም እግረ መንገዳቸው መልእክት ያስተላልፋሉ፡፡

ከዚህ በተጨማሪ ‘Lollat’ ሁለገብ የሙዝቃ መሣሪያ በመሆኗ በተለያዩ ባህላዊ ጨዋታዎች ጊዜ ለአብነት የ‹‹ፊላ›› ጨዋታ ማድመቂያና ማጋጋያ እንዲሁም በለቅሶ ጊዜ ቦግ እንዲል ከፍተኛ ሚና ትጫወታለች፡፡ እንደ መጠኗ ‹‹ሎላት›› የተለያየ ድምጽ ስልምትሰጥ በተለይ ሦስትና አራት አንድ ላይ ሲሆኑ ከእልልታ ጋር ተዳምሮ የሁኔታውን ድባብ እጅግ በማጋጋል የማህበረሰቡን ስሜት ያነሳሳል፡፡

· ‘Rar’//ነጭ ማሽላ//

‘Rar’‹‹ራር›› ወይም ነጭ ማሽላ እንደ ስሙ ነጭ የአገዳ አዝርእት እህሎች አንዱ ሆኖ በጣም ጣፋጭና በዺራሼ ማህበረሰብ ዘንድ ለምግብነት ትልቅ ፋይዳ ያለው እህል ነው፡፡ ማሽላው ከ1.5 ሜትር እስከ 2.3 ሜትር ቁመት የሚያድግ አገዳው እንደ ሸንኮራ በአንጓ የሚከፋፈል ለጥንቅሽነት የሚጠቅም ሲሆን፤ የዛላው ራስ ሹል ሆኖ እስከ 40ሳሜ ዙሪያ ይኖረዋል፡፡

‘Rar’ ወይም ነጭ ማሽላ በማህበረሰቡ አዝመራ ሥርዓት ዝናብ ሲዘንብ ይተከላል፡፡ ማህበረሰቡ የተለየ የእርሻ አስተራረስ ዘዴ የሚጠቀም ሲሆን፤ ይሄውም ሙሉ ማሳው በሦስት ጎራ ይከፈላል፡፡ እነሱም ‘Afaa’፣ ‘Targa’ እና ‘pootaya’/‘pootaytet’ ናቸው፡፡ ስለ ድራሼ ሕዝብ ያስተራረስ ዘዴና ጠቀሜታው በሌላ ርዕስ የምንመለስበት ስለሆነ ላሁኑ በአዝመራ ጊዜ ዘር እንዴት እንደሚተከል እናያለን፡፡ ‘Targa’ ማለት አግድሞሽ የሚል ጽንሰ ሀሳብ ያለው በውስጡ ‘pootaya’/‘pootaytet’ (ጎርጓዳ/ማቆሪያ የሚል እሳቤ አለው) የያዘ ነው፡፡ ስለዚህ ማህበረሰቡ ባብዛኛው እነዚህን ‘Targa’ እና ‘pootaya’ ተከትሎ ዘርን ይተክላል እንጂ አይዘራም፡፡ በዚህ ሁኔታ የ‘Rar’ ዘር በግምት 60ሣሜ ርቀት ማለትም አንድ ተክል በ‘X’ እና በ‘Y’ ምህዋር 60ሣሜ ርቀት ይተከላል ማለት ነው፡፡ ‘Rar’ ሦስትና አራት ሆኖ አንድ ላይ የበቀለው ሥርያማና ድርቅ ተቋቋሚ ከአንድ እስከ ሦስተ ምርት መስጠት የሚችል የአገዳ ዓይነት ነው፡፡

መጀመሪያ ተተክሎ ያደገው ‘Rar’ ለቆረጣ ሲደርስ ምርት ምርቱ ብቻ በማጭድ ይቆረጣል /‘Moqeet’/፤ አገዳው በማጭድ ወይም በ‘Alba’ ዝቅ ተደርጎ ይቆረጣል፡፡ እንደገና በዛ ብሎ ከሥራስሩ የሚነሳው ‘Paqayt’ ለሁለተኛ ዙር ምርት ይሰጣል፡፡ በዚህ ጊዜ አገዳ ነቀላ ይካሄዳል፡፡ ሦስተኛ ዙር የተለመደ ባይሆንም አልፎ አልፎ ዝናብ በበዛበት ዓመት ወይም በችግር ምክንያት አገዳው ሳይነቀል ይቀርና ‘Seytu’ (3ኛ ጊዜ በሰለ) ምርት ይሰጣል፡፡

ነጭ ማሽላ በጣም ጣፋጭ ስለሆነ በሰው ብቻ ሳይሆን በወፎች ዘንድም ተወዳጅ ነውና ዛላው ፍሬ መስጠት ከጀመረበት ጊዜ አንስቶ እስከ ዕለተ ቆረጣ /‘Moqeet’/ ድረስ አንዳንዴ ክምሩም /‘Toorat’/ ይጠበቃል፡፡ ወፍ ጥበቃን ተጋግሶ ለመወጣት፣ ሌሎች ችግሮችን በጋራ ለመጋፈጥ፣ እንዲሁም ወጥ በሆነ መንገድ አንድ ዓይነት እህል መዝራት ውጠታማነቱ እጅግ የጎላ ነው የሚል የማህበረሰቡ የጥንት የጧቱ አስተሳሰብ ነጭ ማሽላም ሆነ ሌሎችን የአዝርዕት ዓይነት በኩታ ገጠም አስተራራስ ሥርዓት ማህበረሰቡ ቀዳሚ ተጠቃሚ ያረጋቸዋል፡፡


ማሳ ላይ ያለ የ‹‹ራር›› እህል

‹‹ራር›› ሆነ ሌሎች እህሎች በመትከል የሚዘሩ ሲሆን፤ ዘር በ‘Qanatha’ (ማንቆርቆሪት) ወይም በኪስ ተይዞ በዝናብ የረሰረሰው መሬት በመውጊያ ‘Ankasset’/አንካሴ፣ ‘Thoothet’ እና ‘Herashot’ ተጭሮ ዘር ይጨመርበትና በእግር እላዩ ላይ ረገጥ እየተደረገ ተከላ ይካሄዳል፡፡ በዚህ መንገድ ተተክሎ የበቀለው ‘Rar’ ወይም ማንኛውም ማሽላ በዛ ብሎ የበቀለ እንደሆነ ሌላው ተነቅሎ ‘Ossa’ ሦስትና አራት ብቻ እንዲቀር ይደረጋል፡፡

‹‹ራር›› በጣም ተፈላጊ እህል በመሆኑ ብዙ ፈተናዎች ይበዙበታል፡፡ ገና ከቡቃያነት ጀምሮ እንደ አገዳ ቆርቆር፣ ‘Olqayt’ ‘Luthot’ ‘Tang’ ‘Farfarot’ ‘Shunqat’ ‘Palaha’ እና በአእዋፋት ተወዳጅነት እንዲሁም ዘር በደንብ በጥንቃቄ ካልተመረጠና የአዝመራ ቀን በውሃ ካልታጠበ እንደ ‘Toff’፣ ‘Yetot’፣ ‘Keltot’፣ ‘Punnatet’ የማሳሰሉት ሊበዙበት ይችላሉ፡፡ በውቂያ ጊዜም ነጭ ብናኝ ‘Raat’ ስላለው የወቂውን ሰውነት በተለይ ብብትና ብሽሽት/ሙሃሂት አካባቢ በጣም ይለበልባል፡፡

‘Kanshira’ ‹‹ካንሽራ››

‹‹ካንሽራ›› የአገዳ አዝርእት እህሎች አንዱ ሆኖ በዺራሼ ማህበረሰብ ዘንድ ለምግብነት ትልቅ ፋይዳ ያለው እህል ነው፡፡ ‹‹ካንሽራ›› እንደ ‹‹ራር›› ከ1.8 ሜትር እስከ 2.6 ሜትር ቁመት የሚያድግ አገዳው እንደ ሸንኮራ በአንጓ የሚከፋፈል ለጥንቅሽነት የሚጠቅም ሲሆን፤ የዛላው ራስ ዘርዘራ ያለ የአገዳ እህል ነው፡፡

‘Kanshira’ በተፈጥሮ ድርቅን፣ ዋግንና ሌሎች በሽታዎችን የመቋቋም አቅም ያለው የአገዳ እህል ነው፡፡ ‹‹ካንሽራ›› እሸቱም ሆነ እህሉ መረር የሚል፣ ምግቡና መጠጡ ቀዝቀዝ ያለ ለመብላት ቆምጨጭ ያለ ሐሞት የሚጠይቅ የአገዳ እህል ነው፡፡ ይሁንና ‹‹ካንሽራ›› ለጤንነት ምቹ እንዲሁም ከቤት ረሃብ (Laot) ማባሪያ መንዶና መድኃኒት ስለሆነ አረረም መረረም ይመረታል፡፡ ወፍ ጥበቃውም እንደ ‹‹ራር›› ከባድ አይደለም፡፡ ‹‹ካንሽራ›› አዝመራ ተከላም ሆነ የአመራረት ሥርዓት ከሞላ ጎደል እንደ ‹‹ራር›› ይሆናል፡፡



· ‘Kur’/Plural = Kurra//እርዳታ//

የዺራሼ ማህበረሰብ በረሃብና ድርቅ ጊዜ እርስ በርስ የሚረዳዱበትና የሚደጋገፉበት ጠንካራ ባህላቸው ‘Kur’ ‹‹ኩር›› ተብሎ ይጠራል፡፡ በማህበረሰቡ ‘Kur’ የሚለው እሳቤ ያለው ለድረቅና ረሃብ ተጋላጭ ለሆኑ ወገኖች እርዳታ ማካፈል ወይም ‘Kur Qot’ ማለት ነው፡፡

ማህበረሰቡ የእህል መክተቻ ጉድጓድ ‘Pollot’ ‹‹ፖሎት›› እንደ ቁጠባ ባንክ የሚጠቀሙ፤ ‘Pollot’ በቁጠባ ሂደት ውስጥ የማይተካ ሚና አለው ብሎ የሚያምንና እንደ ወሳኝ የህይወት ዋስትና ስለሚቆጥሩ አብዛኛውን እህላቸውን በዚሁ የሚከትቱ ናቸው፡፡ ከዚህም የተነሳ የባለጠግነታቸው መጠን የሚለካው ስንት ‘Pollawa’ አለው እንዲሁም ይዘታቸው ምን ያህል ነው፡፡ በ‹‹ፖሎት›› ውስጥ ያለው እህል ሲመናመን ምጥና ራስ ምታት የሚይዛቸው፤ እጅግ ቁጠባ በተሞላ አጠቃቀም ኑሮአቸውን ካልመሩ አደጋ ላይ እንደሚወድቁ ያውቃሉ፡፡

ድርቅና ረሃብ በማህበረሰቡ ዘንድ ምናልባት ቢገቡ እንኳን ትርፍ ‘Pollawa’ ያለቸው ሰዎች የችግሩ ሰለባዎችን ለመርዳት በሥነ ልቡና ሲዘጋጁ፤ የችግሩ ሰለባዎች ተሰብስቦ ያላቸውን ‘Kur’ እንዲያካፍላቸው ይጠይቃሉ፡፡ በጥያቄያቸው መሠረት ያላቸው ሰዎች ለተጎጂ ወገኖቻቸው እርዳታ በማካፈል ከችግሩ ይታደጋቸዋል፡፡ እህል ሲበስል እነዚህ እርዳታ ተካፋዮች ለረጂያቸው በታማኝነት ይመልሳሉ፤ ምስጋናቸውንም ይቸሩታል ማለት ነው፡፡

· ‘Mayira’//‹‹ማይራ››//

‘Mayira’‹‹ማይራ›› ከመቃ ወይም ከሸምበቆ የሚሠራ ባለ ስድስት ‘Fiilet’ ‹‹ፊለት›› ባህላዊ የትንፋሽ የሙዝቃ መሣሪያ ነው፡፡ መቃ በተፈጥሮ እንደ ሸንበቆ ጠንከር ያለ ስላይደለ ወደ ‹‹ፊለት›› ከመቆራረጡ በፊት እንዲጠነክረ በስሱ በእሳት ውስጥ ይለበለባል፡፡ እያንዳንዱ ‹‹ፊለት›› ከቀኝ ወደ ግራ በቁመትም በውፍረትም (ካንድ መቃ የሚቆረጡ ስለሆነ የውፍረት ልዩነት ተፈጥሯዊ ነው) የሚቀንስ ሆኖ፤ ሁለቱ የመጀመሪያዎቹ (‘Tontolit/Kasanit’, ‘Ensharit,) ከሌሎቹ ትንሽ በተለየ ሁኔታ የመርዘም አዝማሚያ ይኖራቸዋል፡፡ የመጨረሻዎቹ ሁለት ‹‹ፊለት›› ‘Fitinfita’ ይባላሉ፡፡ እነዚህ ልዩነቶች ከቀኝ ወደ ግራ ወይም በተገላብጦሽ ሲነፋ የተለያየ የድምጽ ቀለም እንዲሰጡ ያደርጋሉ፡፡

‹‹ማይራ›› መጠንን መሠረት በማድረግ ከትላልቅ ወደ ትናንሽ ‘Hamariya’, ‘Hibariya’, ‘Sirinsita’ ተብሎ በሦስት ይከፈላሉ፡፡ እነዚህ ስድስቱ ‹‹ፊለት›› አንድ ላይ በተለምዶ በሁለት አንዳንዴም በሦስት ቦታ በክር ወይም ከቃጫ በተሠራ ቀጭን ገመድ በማጠላለፍ ‘Tatot’ እንዲሁም እንዳይነቃነቅ በቅንጭብ ወይም በሌላ ሙጫ በደንብ ይጣበቃል፡፡ ሰፋ ሰፋ ያለ ቀዳደ አፍ ያለቸው ላይ ሌላ ከመቃው በጣም በአጭር አጭር የተቆረጠው አንድ ወይም ሁለት አፍ ‘Thoota/Plural = Thootta/’ ይገባለታል፡፡

‹‹ማይራ›› የተለያየ ለዛ ቀለም ያለው ድምጽ የሚሰጥ የሙዚቃ መሣሪያ በመሆኑ ሰዎችን በግለሰብ ደረጃ አሊያም በቡድን ማርኮ የማዝናናት፣ የማነቃቃት፣ የማስደሰት አቅሙ እጅግ በጣም ከፍተኛ ነው፡፡ ስለሆነም ሰዎች በሚሰበሰቡባቸው አካባቢ እንደ ሸንጎ ‘Mora’ በተለይ ደግሞ ሴቶች በህብረት በተቀመጡበት ስፍራ ወንዶች ጎራ ብሎ ማራኪ ለዛውን እየተጨወቱ ከሁሉም በላይ ከለስላሳ ዜማ እንጉረጉሮ ጋር መታጀቡ ሰሚውን በባለጠግነት ድሎት ባህር ውስጥ እንደ ጠገበ ዓሳ በደስታ ስካር ላይ እና ታች እያዋዛ ያንፈረዝዛል፡፡ የ‹‹ማይራ›› ጨዋታ በዓመት ሁለት ወቅት ብቻ መሆኑ ያም በወፍ ጥበቃ ጊዜ ነውና ለመስማት በጉጉት ጆሮ የሚሰጥበት ሌላኛው ገጽታ ነው፡፡ በወፍ ጥበቃ ወቅት በላምባዲና ሊሰበር የማይችል የሚመስለው ጨለማ፣ ቁሩ፣ እንቅፋቱ፣ የመንገዱ ርዝመት እና ሌሎች ተዘርዝረው የማያልቁ ችግሮች ለብቻ መግፋት እንዴት የሚከብድ ነው! ታዲያ በዚህ ጊዜ የእነዚህን መፈጠር የሚያስረሳ አውራው ባህላዊ የሙዚቃ መሣሪያ ተወዳጁ ‘Mayira’ እጅና አፍ አገናኝቶ ብቻ አንድ ሺህ ሆኖ መተመመ ነው፡፡ ብቻውን መንገድ የጀመረው በአውራው ርቀት ተሸጋሪ ሰመመ ከፊት ያለው ቆሞው ሲጠብቁ፤ ከኋላ ያለው ሮጦው ሲደርሱበት በርከት ብሎ በቡድን ‘Luushot’ ሆኖ መንገዱን ይስባሉ፡፡ ፀዳል ገና ሳይፈነጽቅ ማማ ላይ የወጣው ፀሐይ ጠልቃ እስክትገባ ድረስ እዛሁ መሆን ስልችትና እንቅልፍ ወርረው እህል የወፍ ሲሳይ እንዳይሆን ሁለም የማይጠገበውን ‘Hibariya’ ማስመመ የ‹‹ማይራ›› ዋጋና ሚና ከምንም በላይ ከፍ ያለ መሆኑን ያስረዳል፡፡

· ወቅቶችን የመረዳት ዕውቀትና ጥበብ

የዺራሼ ማህበረሰብ የወቅቶችን ጥልቅ ሁኔታ የመረዳትና የመተንበይ ዕውቀትና ጥበብ የሚጠቀሙ፤ ለወደፊት የቤት ሥራቸው አስፈላጊ ግብዓት የሚሆኑ ነገሮችን በማዘጋጀት እንዲሁም በሥነ ልቦናም ጭምር ዝግጅት በማድረግ ይታወቃሉ፡፡ ለዚህ ግንዛቤ እና ትንበያ የሚረዳቸው ደግሞ የከዋክብት ቆጠራና የፀሐይ ቦታ በጥንቃቄ በመመርመርና በማስተዋል ነው፡፡ የማህበረሰቡ አዋቂዎች እንደሚሉት ፀሐይ በተወሰነ ኬንትሮሳዊ (Longitudinal) ርቀት ገደብ ውስጥ የመውጫ ቦታዋን የምትቀያይር አካል ናት፡፡ እንደ ቋሚ ነጥብ (Reference point) የሚወስዱት የመሬት አካላት (Land marks) ለምሳሌ የተራራ ጫፍ፣ በሁለት ተራሮች መካከል ዝቅ ያለ ቦታ ወዘተ የመሳሰሉት ናቸው፡፡ ሌላው የከዋክብት (‘Misinat’, ‘Pakalcha’, ‘Ob Halbayu’, ‘Otindhawsh’, ‘Huritha’) የቦታ ሁኔታ፣ አንደኛው ከሌላው ጋር ያለውን ተቀራራብነትና እርስ በርስ ያላቸው የቦታ አቀማመጥ በትኩረት በመከታተል የመጻዩን ወቅት ሁኔታ ይተነብያሉ፡፡ የዝናብ ሁኔታ ምን መምሰል እንዳለበት፣ አርሶ አደሩ (‘Pehhambit’) ምን ዓይነት እህል መትከል እንዳለበት፣ እንዲሁም ሊመጣ ያለ ችግር ካለ ማህበረሰቡ ቁጠባን ከወዲሁ ማድረግ እንዳለባቸው ጥበባዊ መላምታቸውን ያስቀምጣሉ፡፡

ማህበረሰቡ የዓመትን አስራ ሁለት ወራት በአራት ወቅቶች ከፋፍሎ የከባቢ ሁኔታን ይረዳሉ፡፡ እንደ ማህበረሰቡ ግንዛቤ የፀሐዩና ከዋክብቱ በሁሉም በተጠበቁበት በትክክል መሆን ዓመቱን ጤናማ የከባቢ ሁኔታ እንድኖረው ስለሚያደርግ አስራ ሁለቱ ወራት ወቅቶችን እንደሚከተለው ይገልጻሉ፡፡


· ‘Tang’//ማር//Honey//

‘Tang’‹‹ታንግ›› በሰው ዘንድ በጣም ተወዳጅ ከንብ፣ ከጣዝማ፣ እና ከሌሎች ነፍሳት የሚገኝ ለሰው ልጅ ለምግብነት፣ ለመድኃኒትነት፣ ወዘተ የሚጠቅም ጣፋጭ ነገር ነው፡፡ ‹‹ታንግ›› ወይም ማር የገቢ ምንጭም ስለሆነ ለማግኘት የተለያየ ማህበረሰብ የተለያየ የማነብ ዘዴንና ስልትን ይከተላል፡፡ የዺራሼ ማህበረሰብም ከእርሻ ሥራ በተጓዳኝ የንብ ማነብ ሥራንም ያከናውናል፡፡ ስለሆነም ማርን በሁለት መንገድ ያገኛል፡፡

የመጀመሪያውና ዋናው የንብ ቀፎን አበጃጅቶ፣ ሰቅሎ በረጅሙ መንገድ ማርን መቁረጥ ነው፡፡ ሁለተኛውና የባለ ዕድለኛው ሳይለፉበት ማርን በዋሻ ወይም በገደል ወይም በውስጠ ክፍት ግንድ ወይም በመሬት ውስጥ ወዘተ ቦታ ካገኙ መቁረጥ ነው፡፡ ከቀፎ የሚቆረጠው በህዝቡ ዘንድም ‘Tang Hant’/የንብ ማር ተብሎ ሲጠራ፤ ከዚህ ውጭ ያለው ቀባ/ቃባ/ ‘Toll’፣ ጣዝማ ማር ‘Tang Tammat’፣ እና ‘Tang Pambanat’ ተብሎ ይጠራል፡፡

ንብ በተለምዶ ጠቆር ያለ/‘Katib’ ወይም ጠየም ያለ/‘Sorotu’ ሲሆን፤ በመንጋ ደረጃ ብዛት ያለው ‘Katib Hant Kan’፣ መካከለኛው ‘Sorotu Hant Som’ እና በጣም አነስተኛው ‘Pohiya’ ይባላል፡፡ ማርም እንደ ንቡ ቀለም ጠቆር ወይም ነጣ ያለ ይሆናል፡፡

የሚመረተው የማር ምርት መጠን የሚወሰነው በቀፎ/‘Kagurt’ ይዘትና በየማር እንጀራ ‘Qa’a/Qa’ana’ አደራደር ሁኔታ እንደዛውም ጥራቱና ጣዕሙ በጊዜና ንቡ ለቅስምና ግብዓት በተጠቀመው ይወሰናል፡፡ በቂ ግብዓትና ምቹ ሁኔታዎች ሲገኙለት ቀፎን ጥም ሲደረድር፤ በተቃራኒው ሲሆን በመሃከል ክፍት ቦታ ትቶ (ወላቃ ወይም ‘Poshola’ ይባላል) ጫፍና ጫፍ ይሞላል፡፡ አንዳንዴ በድንብ ያልደረሰ ማር/‘Tilot’ ወይም ከትክክለኛ ጊዜው አለፍ ብሎ ወደ እጭነት ደረጃ ያደገ/‘Dhalt’ ወይም ወለላው ሙሉ በሙሉ በንቡ ተቀስሞ ያለቀበት የማር እንጀራ/‘Koga’ በማር ቆረጣ ጊዜ ያጋጥማል፡፡

‘Ol Qaba/Or Qaba Qarqarsat//የመረዳጃ ማህበራት//

የዺራሼ ማህበረሰብ ከጥንት ጀምሮ እርስ በርስ የሚረዳዱበትና የሚደጋገፉበት መደበኛና መደበኛ ያልሆነ ማህበራዊ የመረዳጃ ህብረት ባህል አላቸው፡፡ እነዚህ የመረዳጃ ማህበራት ለተለያየ ህብረተሰባዊ ጉዳዮች ማገዣ፣ መረዳጃ፣ ማጽናኛ፣ ማበረታቻ፣ ወዘተርፈ አገልግሎት የሚውሉ ናቸው፡፡ ለምሳሌ ያክል በለቅሶ፣ አረም፣ ቁፋሮ፣ አጨዳ፣ ውቂያ፣ ፈትል፣ ከብት ሲሞት፣ ቤት ስራ፣ ሰርግ እንዲሁም እንደ ዕቁብ ገንዘብ ሰብስበው በየተራ በመውሰድ እርስ በርስ የረዳዱበታሉ፡፡

ማህበረሰቡ እነዚህን ትሩፋታዊ እሴቶችን በሦስት ጠቅለል ባለ መልኩ ይሳተፍባቸዋል፡፡ የመጀመሪያው አንድ ሰው በማህበረሰብ ውስጥ እስካለ ድረስ በዘላቂነት የሚሳተፍባቸው ናቸው፡፡ እነሱም ‘Qayit’፣ ‘Possunta’፣ እና ‘Kaffumat’ ናቸው፡፡ በሁለተኛ ደረጃ አንድ ሰው ማህበራዊ መረዳጃ ህብረቶች በስምምነት ለጊዜያዊ ችግር መፍቻነት ሲመሠረቱ በፈቃዱ የሚሳተፍባቸው ናቸው፡፡ እነዚህም ‘Kala’፣ ‘Dha’et’፣ ‘Ediret’፣ ‘Equbet’፣ ‘Mabar’፣‘Awlanta’ እና ‘Helt’ ናቸው፡፡ በመጨረሻም ግን ቀላል ይማይባል ሚና የሚጫወተው እንዲሁ በልመና ብቻ የሚደረግ መረዳጃ ህብረት ውስጥ መሳተፍ አለበት፡፡ ዋና ዋናዎቹም ‘Dhingam’ (ደቦ፣ ወንፈል, ወበራ፣ ጅጌ) እና ‘Erba’ ናቸው፡፡

የድራሼ አስተዳዳር መዋቅር ውስጥ አንዱ የሆነው ቀበሌ ወይም ‘Haft’ በቀጠና ‹‹ቃጣና›› የተሸነሸነ ሲሆን፤ እያንዳንዱ ‹‹ቃጣና›› በ‘Qayit’ ሥርዓት ይተዳደራል፡፡ በዚህ በቀጠና አስተዳደር ሥርዓት ውስጥ ያሉ በሙሉ (ዘጠኙም ጎሳ ባጠቃላይ) አባል፤ ዕኩል መብትና ግዴታ ሲኖራቸው፤ እንደየዕድሜ ክልላቸው ግን የሚጠበቅባቸው ድርሻም ይለያያል፡፡ ህጻናትን፣ አካል ጉደተኞችን፣ ልጆችንና አዛውንትን ሳይጨምር ከወጣትነት ዕድሜ ክልል እስከ ጎልማሳ ድረስ ያለው እንደየጾታቸው ከፍተኛ ተሳትፎ ይጠበቅባቸዋል፡፡

ስለሆነም ዋና ዋና ሥራዎቹ ወንዶች የታመመ ሰውን ህኪምና ቦታ ማድረስ፣ የቀብር ሥነ ሥርዓትን መፈጸም ማስፈጸም፣ እና ሌሎች የሰው ኃይል የሚጠይቁ ሥራዎች እንዲሁም ማንኛውም አስተዳደሩ የሚጠይቃቸውን ሁሉ ሲሰሩ፤ ሴቶች ደግሞ ለቅሶ ቤት ውሃ መቅዳት፣ እንግዳን ማስተናገድና ሌሎችንም ሥራዎች ላይ ይሳተፋሉ፡፡ እያንዳንዱ አባወራ/እማወራ ለመረዳጃ የሚሰበሰበውን ‘Kontat’ በእህል አሊያም በገንዘብ ይከፍላል፡፡ በእነዚህ ውስጥ አለመሳተፍ ከትንሹ ቅጣት ‘Madha’a’ እስከ ከሥርዓቱ መታገድ ያስከትላል፡፡

‘Possunta’ ‹‹ፖሱንታ›› በለቅሶ ጊዜ ባብዛኛው በዝምድና አንዳንዴ በጎረበት መረዳጃ ሰብስበው በጋራ ተቀምጦ የተገዛውን ማዕድ የሚበሉበት የሚጠጡበት ማህበራዊ ህብረት ሲሆን፤ ‘Kaffumat’ ‹‹ካፉማት›› የሚባው ዝምድና የሚል እሳቤ ሲኖረው ከተለያየ አካባቢዎች ያሉ (ድራሼ ምድር) የአንድ ጎሳ ሰዎች የሚመሠርቱት ህብረት ነው፡፡ ዋና ዓላማውም ጎሳ እርስ በርስ እንዲተዋወቅ፣ በመካከላቸው የሚፈጠሩ ችግሮችን በጋራ ለመፍታት፣ የተቸገረን በገንዘብ ለመርዳት፣ ተመክሮ ከጥፋት የማይመለስ ሰው ወጊድ እንዲሆን፣ እንዲሁም የጎሳ አስተዳደር ጠንካራ ዓምድ ሆኖ በዘላቂነት እንዲቀጥል ነው፡፡ አንድ ወይም ሁለት ሰዎች በሳምንታት (3-6 ሳምንታት) ተራ ወስዶ በድራሼ ሕዝብ በጣም የሚወደድው ምግብና መጠጥ የሆነውን ‹ፓርሾት› ይጠምቃሉ፤ እድምተኛውም መዋጮውን ከፍሎ የተዘጋጀውን ማዕድ ተጋርቶ፤ ውይይት አድርጎ ቀጣይ ተራ ሰጥቶ ይለያያሉ፡፡

‘Kala’ ‹‹ካላ›› የተወሰኑ ሰዎች (ሴቶች ለብቻ፣ ወንዶች ለብቻ) (10-30 ሰዎች) በስምምነት የሚፈጥሩት ማህበራዊ ህብረት ሆኖ እያንዳንዱ ቤት ስራ ለከወኑበት ምንዳ ወስደው በገንዘብ ያዥያቸው ‘Kadhaya’ በኩል ያጠራቅማሉ፡፡ አባል ለሆነውም ላልሆነውም በአነስተኛ ገንዘብ ማንኛውም ስራ ይሰራሉ፡፡ የሚከፈለው ምንዳ እንደ ስራው ጥንካሬና አባል መሆን አለመሆን ይለያያል፡፡ በዓመት ሁለት ጊዜ ያክል አንድ ላይ ተቀምጠው አንጡራቸውን ኦዲት ‘Shallag’ ያደርጋሉ፤ ክፊያውንም አሻሽለው ይወስናሉ፤ በቂ ገንዘብ ሲኖራቸው የአንድ ግለሰብ ቤት ለምነው በሬ፣ ፍየል እና ስጋ ገዝተው በ‹‹ፓርሾት›› ይበላሉ፤ ይጠጡማል፡፡

‘Dha’et’ የሚለው ሀሳብ ሰዎች (3-60 ሰዎች) ለተወሰነ ጊዜ ተስማምቶ የሚፈጥሩት ህብረት ሲሆን፤ እያንዳንዱ ቤት ምናልባትም ተመሳሳይ ተግባር ይከውናል፡፡ ከዚህም የተነሳ ወበራ (የውቂያ)፣ የአረም፣ የፈትል፣ የእንጨት ለቀማ፣ የጎጆ ቤት መቀለሻ፣ የአጨዳ፣ ወዘተ በመባል ይታወቃል፡፡ አንዳንድ ጊዜ አህያ ብቻ በመላላክ የ‘Dha’et’ መረዳጃ ህብረት ይሰራል፡፡

‘Ediret’ የሚባለው ወጣት ወንዶች በርከት ብሎ (እስከ 100 የሚሆኑ) በዋናነት ለሰርግ ዓላማ የሚመሠርቱት ህብረት ሲሆን፤ በባህሉ መሠረት አግቢው ወንድ ለሴት ቤተሰብ እንዲያገለግል የሚጠየቀውን አገልግሎት (ቁፋሮ፣ ቤት መቀለስ፣...) ህብረቱ ይሰራል፤ ሙሽሪትን ይከባከባል (ሚዜ በመሆን፣ የጸጉር ቅቤ መግዛት፣…)፣ በሰርግ ቀናት ሰርጉን በማጀብ የሚረዳ፤ የተደራጀ ደንብም ያለ ማህበር ነው፡፡

‘Equbet’ ሴቶች (አንድ ወይም ሁለት ወንድ ይኖርበታል) የሚፈጥሩት ማህበራዊ ህብረት (50-100) ሲሆን፤ ዋና ዓላማውም ጥጥ መፈተል እንዳለ ሆኖ ሴቶች ለብቻቸው አንድ ላይ ተቀምተው እየተጨዋዋቱም፣ ባህላዊ መጠጥ ‹‹ፓርሾት›› እየጋቱ የመዝናኑበት፣ ከማጀት ሥራ ወጥተው ተናፍሰው አእምሮአቸውን የሚያሳድሱበት ነው ማለት ይቻላል፡፡

‘Mabar’ ‹‹ማባር›› ወንዶች ለገንዘብ መሰብሰቢያነት ሲባል የሚመሠርቱት ማህበራዊ ህብረት ሲሆን፤ እያንዳንዱ ማህበርተኛ በሳምንታት (3-5) ተራ ወስዶ ባህላዊ መጠጥ አዘጋጅቶ ማህበርተኛውን የሚያስተናግድበት፤ የመዋጮው ገቢ የሚየገኝበት ተደራጅቶና ደንብ ያላው ህብረት ነው፡፡

‘Awlanta’ ልክ እንደ ‹‹ዕድር›› ሴቶች ለሰርግ ዓላማ የሚፈጥሩት ህብረት ሲሆን፤ ዓላማው ተጋቢዎችን በቁሳቁስ መርዳት ሆኖ ሴቶቹ ተሸቀርቅሮ ከቀኑ 7 ሰዓት በኋላ ሙሽሪት ጋር ገብቶ በ‘Shagla’ ዙሪያ የወንዱን ሁኔታ እየጠየቁ ጎበዝ ከሆነ የሚያሞግዙበት፣ አለበለዚያ እየነቀፉት የሚያጣጥሉበት ነው፡፡ በዚሁ አጋጣሚ ለወንዶች እይታ ተጋላጭ ዕድል ያገኛሉ፡፡

‘Heelt’ ‹‹ሄልት›› የሚባው ሰዎች ክብትን ወይም ፍየልን ተራ በተራ ለማሰማራት የሚፈጥሩት ህብረት ነው፡፡ እያንዳንዱ አባል በተለምዶ ሦስት ቀናት አግዶ ለቀጣይ ተረኛ ያሰረክብና ቀጣይ ዙር እስኪ ደርሰው የግሉን ሥራ በነጻነት ይሰራል፡፡

‘Dhingam’ የሚባለው ደግሞ ከማህበረሰቡ እሴቶች አንዱና ወሳኝ ሲሆን፤ በተለያየ መልክ እገዛ የሚፈልገው ግለሰብ ጎረበቱን፣ ዘመዱን፣ ጓደኞቸቹን ወዘተ በልመና እንደ ደቦ፣ ወንፈል፣ ጅጌ የሚረዳበት የተለመደ ማህበራዊ ተሳትፎ ነው፡፡ በዚህን ጊዜ ተረጂው የዕለት ስንቅ እንደ ‹‹ፓረሾት››፣ ‹‹ማና››፣ ‹‹ቃላላ››፣ ‹‹ሀርሶት››፣ ወዘተ በማዘጋጀት ሆዳቸውን ይችላል፡፡

‘Erba’ ‹‹እርባ›› የሚለው እሳቤ መርዳት ሲሆን፤ ከብት ሲሞት ስጋውን በአነስተኛ ዋጋ በመከፋፈል፤ አንዳንዴ ደግሞ እንደ አህያ፣ በቅለሎ ሲሞቱ ትንሽ ብር እየሰጡ ይረዳሉ፡፡

‘Olmaca’*** ‹‹ኦልማጫ›› የሚለው እሳቤ ሰዎች ከብዙ ድካም በኋላ ያፈሩትን አንጡራ ሀብታቸውን ጨዋነትና መከባበር በተሞላበት ማለትም በጣም እርስ በርስ የሚከባበሩ ሰዎች በጥቂት በጥቂት ሆነው (5-10 ሰዎች) ተስማምቶ በህብረት በመቀመጥ ረጋ ብሎ የሚያመነዥጉበት፣ የሚያላምጡበት ማህበራዊ እሴት ነው፡፡ በዚህ ህብረት ውስጥ የሚሳተፉት ብዙን ጊዜ በዕድሜ ጠና ያሉ ባለጠጋ ባልና ሚስት ሲሆኑ፤ የእረፍት ጊዜ (የሥራ ወቅት ያልሆነ ተመርጦ) መረባበሽ በሌለበት ስፍራ ተቀምጠው በተረጋጋ ስሜት ውስጥ ሆነው ከጠዋት እስከ ምሽት ስጋውን ከ‹‹ፓርሾት›› ጋር ያላምጣሉ፡፡ በዚህን ጊዜ መጣላት፣ መነቋቆር፣ መነዛነዝ አይቻልም፡፡ ከሌሎች ማህበራዊ ህብረቶች የሚለየው የእረፍትና ቀድሞ የደከሙበትን አንጡራ ሀብት መበያ፣ ማጠፊያ ጊዜ ነው፡፡

4. Ogat Qedha’a Dhirahsat//የዺራሼ ጋብቻ ወግ//

የሰው ልጅ ከሚያልፍባቸው ተፈጥሯዊ የህይወት ምዕራፎች ዋና ዋናዎቹ መወለደ፣ ማደግ፣ ማግባት፣ መውለድ እና በመጨረሻም መሞት ናቸው፡፡ እነዚህ ምዕራፎች ብዙሃኑ የሚጋራቸው ናቸውና አንድ ሰው ተወልዶ ካደገ በኋላ ለማግባት የሚያስብበት ዕድሜና ሁኔታ ይለያይ ይሆናል እንጂ ማግባት ግደታው ነው፡፡ ማግባትና መጋባት ሁሉንም ማህበረሰብ ያመሳስሉ እንጂ እያንዳንዱ ማህበረሰብ ጋብቻን የሚፈጽምበት ወግና ሥርዓት ይለያያል፡፡

የድራሼ ማህበረሰብም እንደ ሌላው ማህበረሰብ ከጥንት ጀምሮ የጋብቻ ሥርዓትን የሚፈጽምበት ወገና ባህል አለው፡፡ የማህበረሰቡ የጋብቻ ሥርዓት አፈጻጸም የራሳቸው ማንነት ገላጭ፤ ደግሞም ከሌሎች ተጋሪ ማህበረሰቦች ጋር የሚያስተሳስር ሲሆን፤ እንዲሁ በጥቅሉ ሲታይ በሦስት አብይ እረስ በርስ የተከረነቱ ምዕራፍ ደረጃዎች ይኖሩታል፡፡ እነዚህም የትጭጭት ጊዜ//‘Helba Rabata’//፣ የቅድመ ሙሽሪትነት ጊዜ//‘Helba Qoramat’// እና የጫጉላ ጊዜ//‘Helba Usikat// ተብሎ ይጠራሉ፡፡ የእያንዳንዱን ምዕራፍ ዝርዝር ሁኔታ አብረን እናየለን፡፡

ማህበረሰቡ ከወግና ሥርዓት ውጭ ተያይዞ መጥፋት፣ ከጋብቻ በፊት የግብረ ሥጋ ግንኙነት መፈጸም እና ሳያገቡ ዲቃላ ልጅ መውለድን በአጽእኖት ይቃወማል ያወግዝማል፡፡ ታዲያ እንዲህ የጠበቃ ወግ እያላቸው አልፎ አልፎ ከሥርዓት ውጭ የሚንቀሳቀሱ መኖራቸው እጅግ የሚያሳዝን ጉዳይ ነው፡፡

· ‘Helba Rabata’//የእጮኝነት ጊዜ//

‘Rabata’ ‹‹ራባታ›› የሚለው ሀሳብ ማጨት፣ መያዝ ማለት ሲሆን፤ አንድ ወንድ አይቷት ደስ ልቡ የደነገጠባት፣ ወይም ቀድሞም የሚያቃት አሊያም ቤተሰቦቹ የመረጡለትን ለነገ የትዳር ጓደኝነት ከቤተሰቡ ጋር ተወያይቶ ይወስናል፡፡ በውይይት ወቅት አራት አንኳር ጉዳዮች በመስፈርትነት ይታያል፡፡ እነርሱም ጎሳዋ፣ ለሥራ ታታሪነቷ፣ አመለካከት ወይም መልካም ስብዕናና በማህበረሰቡ ዘንድ ተቀባይነት ስላጡ ምድራዊ ማንነቶች ናቸው፡፡ ቁንጅናና ውቤት የትኩረት ስበቶች አይደሉም፡፡ እናም እነዚያን መስፈርት ያሟላች ሴት ከሆነች ወንዱ ጓደኞቹን አስተባብሮ ውሃ ስትሄድ ስትመለስ ፍለጋውን ይቀጥላል ማለት ነው፡፡

በመጀመሪያ ያገኙአት ቀን ባለጉዳዩ የሆነው እጆቿን ያዝ ያረግና ለግብረ አበሮቹ ይለቃታል፡፡ በዚህ ትዕይንት ማን እየጠየቃት እንደ ሆነ ትረዳለች ማለት ነው፡፡ ሁለተኛ በመጡ ቀን ፍላጎት ካላት ተረጋግቶ ማውራት ይጀምራሉ፤ ቀጣይ ሲመጡ መያዣ ‘Rabot’ ይዞ እንዲመጡ ትነግራቸዋለች፡፡ ስለዚህ በቀጣይ ግንኙነት የሚሰጣት መያዣ ‘Rabot’ ከቀጭኔ ጭራ የተሠራ ‘Qacinet’ እና/ወይም ብር ሊሆን ይችላል፡፡ ታጭታለች በቃ፡፡

በልጅቷ ስምምነት የመጀመሪያ ሽምግልና ይላካል፤ ቤተሰብ የሚያወቀው ታሪክ ስለሌለ የማን ልጅ እንደ ሆነ ይጠይቃል፣ ሽማግላችን ይሸኙና ነገሩ ከሷ ስለመሆኑ በአክሰቷ ያስጠይቋታሉ፤ ሁለተኛና ከዚያ በላይ ዙር ሲመጣ ቤተሰቦቿ አቅጫጣ ያስቀምጣሉ፤ ልጅ ከሆነች ገና ልጅ ናት ይህንን ያህል ዓመት ይጠብቅ፣ የደረሰች እንደሆነ ይስማማሉ፡፡ አለበለዚያም ከነአካቶ ልጃችንን ለዚያ ቤተሰብ አንሰጥም ሊሉ ይችላሉ፡፡

በባህሉ መሠረት እጮኛሞቹ ተስማምተው ይጠልፋታል፤ ለቤተሰቦቿ ሽምግልና ይላከካል፤ አሁንም በአክስቷ በኩል አንደበቷ ይጠየቃል፡፡ መልሱ እሺ ፈቃዴ ነው ግን ቤተሰቦቼ ጋ ገባለሁ፣ ፈቃዴ ነው ወደ ‘Qoramat’ ሄዳለሁ፤ አሊያም እንቢ ፈቃዴ የለበት ይሆናል፡፡ መልሷ ወደ ‘Qoramat’ እሄዳለሁ ከኾነ እንደ ማህበረሰቡ ወግ አባት ሴት ልጁን በጋብቻ ቀን ስለማይሰጥ (ክልክል ወይም ነውር ነው) ወይም ሴት ከቤቷ ወጥታ ስለማትዳር እሷ ወደ ሁለተኛው ምዕራፍ ወደ ወንዱ ወገን ቤት ትገባለች፤ ውንዱ ለቤተሰቦቿ ጥሎሽ (ገንዘብ፣ ከብት) ይጥላል፣ በባህሉ ልክ ያገለግላቸዋል፡፡

· ‘Helba Qoromat’//Pre Bride Culture//

‘Qorom’ ‹‹ቀሮም›› የሚለው ጽንሰ ሀሳብ አንድን ሰው ቤት ውስጥ ከፍተኛ እንክብካቤ እየተደረገለት ማቆየት ማለት ነው፡፡ በድራሼ ባህል ሴት ልጅ ታጭታ የባህሉ ወግና ሥርዓት የሚጠይቀውን ሁሉ የወንዱ ወገን ለሷና ለቤተሰቦቿ ከፈጸመ በኋላ ቀጥታ ወደ ወንዱ ቤት አትወሰድም፡፡ በወንዱ ወገን ቤት በትንሹ ከስድስት ወራት እስከ አንድ ዓመት ተቀምጣ ትንከበከባለች፡፡

ስለሆነም የድራሼ ማህበረሰብ ወንድ ልጅ አንዲትን ሴት ልጅ ካጫት ጊዜ ጀምሮ በውድም በግድም ልጅቱን ‘Qorom’ የሚል የባህሉ እሴት ያሳስበዋል፡፡ ስለዚህ እጮኛውን በቤቱ ተቀብሏት የእንክብካቤውን ሂደት ‘Qoromat’ ‹‹ቆሮማት›› በሥርዓት የሚያከናውንለትን ወገኖቹን ቤት በሕሊናው ማሰብና ማሰላሰል ይጀምራል፡፡ መልካም ምስክርነት ያላቸው፣ የሚዋደዱ፣ ትህትና የለበሱ፣ በተጨማሪ ደግሞ ሀብታም የሆኑን መዘርዘርና ከቤተሰቡ እንዲሁም ከእጮኛው ጋር ማማከር ይጀምራል፡፡ ከሁለቱም ይሁንታ ያገኘ ቤተሰብን ለምኖ እንዲንከባከባት በአደራ ያስረክባቸዋል፡፡

ቅድመ ሙሽሪትነት ሂደት የሚያካሂዱ ቤተሰብ ልጅቱን ከተረከቧት ጀምሮ ቅድመ ሙሽሪት ከራሳቸው ጋር ያለማምዳሉ፣ ያጫውታሉ፣ በቤት ውስጥ የምትፈልገውን በነጻነት እንድትጠቀም፣ እረፍት እንድታደርግ ይመክራሉ፡፡ አስፈላጊውን ሁሉ ውሃን ጨምሮ ያቀርቡላታል፡፡ በዚህን ጊዜ የነገው ሙሹራ ከሚሳተፍበት ህብረት ‘Ediret’ ሦስት ወንድ ሚዜዎቿን ትሰይማለች፡፡ እነዚህ ሚዜዎች ከወንድ ጓደኛዋ በኩል የሚያስፈልጋትን ነገሮች ሁሉ እንደ አልባሳት፣ የጸጉር ቅቤ፣ ወዘተ ያቀርባሉ ያመቻቻሉ፡፡ ከ‘Ediret’ መዋጮንም ይሰበስባሉ፣ በሁለቱ የነገ ተጋቢዎች መካከል መረጃን ያለዋውጣሉ፡፡

ልጅቱ በአደራ በተቀመጠችበት ቤት ጧት ጧት ግቢውን ሙሉ ሙልጭ አርጋ ትጠርጋለች፣ ጥጥ ትፈትልላቸዋለች፣ ምግብ ትሠራለች፣ በአጠቃላይ የቤት ውስጥ ሥራ ሁሉ ታግሳቸዋለች፡፡ በባህሉ ወግ መሠረት ሰዎች ከትናንሽ ጀምሮ እስከ ትላልቅ ወደ እርሷ ይመጣሉ፣ በተለያየ መልክ ይቀልዱቧታሉ (‘Haybat’, ‘Sadhat’ ወዘተርፈ እያሉ)፣ ሁሉንም እንደ አመጣጣቸው ታስተናግዳለች ታስደስትማለች፡፡ በተለይ ምሽት ምሽት ሁለ ሰዎች በዙሪያዋ ተሰብስቦ ይቀልዳሉ፣ ባህላዊ ጨዋታ ይጫወታሉ፣ ያዝናናታሉ፣ እሷ ክራር ትመታላቸዋለች የማትችል ከሆነ ያለማምዷታል፡፡

‹‹ቆሮማት›› በእንዲህ ዓይነት ሁኔታ ሲኾን በርካታ ሥነ ልቦናዊ፣ አካላዊ እና ማህበራዊ ጠቀሜታዎችን ለሙሽሪት ያጎጽፋል፡፡ ሙሽሪት በተመቻቸላት አካባቢ ውስጥ ሆና ንጽህናዋን በድንብ ትጠብቃለች ጥሩ ጥሩ ምግቦችን ትመገባለች፡፡ አዲስ ቤተሰብ ጋር ራሷን ለማላመድም ሆነ ዝቅ ብላ ሌላ ቤተሰብን ለማገልገል በምታደርገው ትግል ውስጥ ትህትናን፣ ታዛዥነትን፣ መቻቻልን፣ መከባበርን፣ የአገልጋይነት ስሜትን ስትማር፤ በሌላ በኩል ደግሞ ሰዎች ወደ እርሷ ቀርቦ አብሯት መጫወታቸው በሌሎች ዘንድ ተወዳጅ፣ ክብርት፣ ተፈቃሪ መሆኗን ስትረዳ፤ ከነዚህ ሰዎች ጋር ስትውል አንዳቸውንም ሳታስከፋ ማሳለፋ፤ ማህበራዊነት እንዴት መስተናገድ እንዳለበት በተግባር ተፈትና ትማራለች ታልፍማለች፡፡ ከዚህም አልፎ ተርፎ ሙሽሪት ከስድስት ወራት እስከ ዓመት በእንዲህ ሁኔታ ተቀምጣ ስትቆይ በአካለ ሰውነቷ ዳብራና ፋፍታ፤ ምናልባትም ተጠልፋ ወደዚህ ስፍራ ስትመጣ ዕድሜዋ አስራ ስምንት ዓመት ያልሞላት እንደሆነች አሁን ዕድሉን ተጠቅማ በቀጣይ ሕይወቷ ያለ ስጋ እንድትኖርም ያግዛታል፡፡ በዚህ መልክ ያካበተችው ልምድ ነገ ባል ቤት ስትሆንም እናትነት፣ እንግዳ ተቀባይነት፣ ሰው አክባሪነት፣ ወዘተ አዲስ እንግዳና ዱብ እዳ ሆኖባት እንዳትቸገርም ይረዳታል፡፡

ሌላው ገጽታ በዚህን ጊዜ ሙሽራ ሊሆን ያለው ወንድ በኢኮኖሚም ሆነ በሌሎች ዝግጅቱን ያጠናቅቃል፣ የሰርግ ጥሪ መልዕክት መድረስ ላለበት ያድርሳል፡፡ የሙሽሪት ቤተሰብም ልጃቸው ላይ መቆም ላለባቸው ጥሪ ያደርሳሉ፡፡ የሰርግ ዝግጅት ግን የለም፡፡ በባህሉ መሠረት እዚህ ቤት መምጣት ለጊዜው የተከለከለው የጋብቻ ቀነ ቀጠሮ ሲደርስ ሙሽሪትን ለመውሰድ በጉጉት የሚጠባበቀው ሙሽራ ከነሰርገኞቹ ቅዳሜ ምሽት እዚህ ቤት ዳግም ለመጀመሪያ ጊዜ ከች ይላል ማለት ነው፡፡

· ‘Helba Qe’dhot ne Helba Usikat’// የሰርግ እና ጫጉላ ጊዜ//

በሦስተኛው ሰርግና ጫጉላ ምዕራፍ የሰርግ ዝግጅት በወንዱ ቤተሰብ ተደርጎ ሙሽራው እድሩንና ሌሎች አጃቢዎችን እስከትሎ ቅድመ ሙሽሪትን ወዳስቀመጠበት ቤተሰብ በምሽት ከተፍ ብሎ ሙሽሪትን በኃይለኛ ጭፈራና ፈንጠዚያ አሳጅቦ ቤቱ ይወስዳታል፡፡ ሙሽሪት አግጣና ተሞሽራ ጸጉሯ በቅቤ ተለብጦ፤ ወፍራም ጥንድ ጋቢ ‘Korret’ ተከናንባ፣ በጥቂት ሸኚ ሴቶችና ሚዜዎቿ ተከብባ፣ ቀስ እያለች ስትሄድ ሰርገኛው በሁለት ጎራ ተከፍሎ ወደፊትና ወደኋላ ሲተላለፍ ገፍተር ገፍተር እያረጋት ወደ ቤት ይደርሳሉ፡፡ ከልጁ ቤተሰብ በወጉ መሠረት ነገያቸውን የሚመሩበት ድርሻ ‘Kodha’ ተሰጥቷቸው ወደ ጫጉላ ቤት ያመራሉ፡፡ ወንዱ በር ላይ ከተቀመጡ ከጓደኞቹዎች ጀርባ ተቀምጦ ከመች መች ወደ ሙሽሪት ይለቁኛል እያለ ናፍቆትና ፍርሃት በተደባለቀ ስሜት ቁና ቁና ሲተነፍስ፤ አጃቢ ሴቶቹ ለቆ ሲወጡ፣ ሚዜዎች ወግንና ደንብን በጥብቅ ለሙሽሪት አስገንዝቧት፣ ሙሽሪት መቀነት መፍቻ ሦስት ብር ‘Dhagara’ በማህበረሰቡ ዘንድ ‘Kubeet’ ተብሎ የሚጠራውን ሰጥቷት ወደ ውጭ ሲወጡ፤ በናፍቆት ጡዘት የናረው ሙሽራ በጎን ጎናቸው ሰተት ብሎ ገብቶ በሩን ወደኋላ ይዘጋል፡፡ ሚዜዎችና ወጣቶች ጫጉላ ቤቱን ከብቦ የወንዱ ወደ ውጭ ወጥቶ ብልቱን እንዲያሳያቸው የሚጠባበቁት እርሱ ብቅ ሲል የ‘Shagla’ ጨዋታን ይጀምራሉ፡፡ ብልቱ ተገትሮ ከሆነ ሙገሳን፣ አድናቆትን ገልጾ ጨዋታው ከሴቶች እልልታ ጋር ድብልቅልቅ ብሎ ሲደራ፤ በተቃራኒ ሲሆን ኤጭ ‘Sagot’ እያሉ ከጨዋታው ጀምሮ ሰርጉ ሁሉ ቀዝቀዝ ይላል ማለት ነው፡፡

በዚህ መልክ ቅዳሜ ማታ የተጀመረው እሁድ ቀኑን ሙሉ ሲጨፈር፣ ሲወደስ ይዋላል፡፡ የሙሽራዋ መረዳጃ ማህበር ‘Awlanta’ ተሽቀርቅሮ ከቀኑ 7፡00 ሰዓት አካባቢ ሲመጡ፤ ዕድርተኛው ሰርጉን ሞቅ ደመቅ በማድረግ ሙሽራውን በትከሻ ይሸከሙና ‘Halakasha’ በ‘Hayloga’ ጭፈራ አቀባበል ያረግላቸዋል፡፡ ወደ 11፡00 ሰኣት አካባቢም ተመሳሳይ ትዕይንት በማሳየት እንዲሁም ከጓደኞቿ ጋር እስክታውን በማውረድ አሸኛኘት ያረግላቸዋል፡፡ መሽራው በትከሻ ላይ እያለ ‹‹ፓርሾት›› በባህሉ ጥበብ በተሰራው መንቀል ‘Wallet’ ተሞልቶ እንዲቀምስ ይደረጋል፡፡ ሰኞ ዕለታ ዳሱ ፈርሶ እድምተኛው ወደየቤቱ ሲሸኝ ቤተሰብና ጥቂት ጓደኞቹ ከእነሱ ጋር ይቀራሉ፡፡

በዚህ ሁኔታ የተጀመረው ሰርግ ወደ ሦስተኛው ምዕራፍ ወደ ሆነው ጫጉላ ሕይወት ያመራና ሙሽራው ለሳምንታት ሙሽሪት ግን ለሦስት ወይም ለአራት ወራት በቤት አረፍ ብላ ተቀምጣ አስፈላጊ እንክብካቤ እየተደረገላት ድልቅቅ ሕይወቷን ታጣጥማለች፡፡ ይህ ምዕራፍ የ‘Urusum’ ተብሎ ሲጠራ፤ እሳቤውም ጉዳት የደረሰበትን ወይም ወላዲትን ወይም የታመመን ተጠግኖ ወደ ጤነኛ ማንነቱ እስኪ መለስ የተመጣጠነ ምግብ የሚሰጥበት ሥርዓት ነው፡፡ ጭብጥ ሀሳቡ የመጀመሪያው ግብረ ሥጋ ግንኙነት የሚደረገው በጉልበትና በኃይል በትግል ስለሆነ ሙሸሪት በሙሽራው በተለያየ መልኩ ጉዳት ይደርስባታል የሚል ነው፡፡ ለዚህም ነው ወንዱ ቢደፍራትም ባይደፍራትም ሙሽሪት በሁለት ሰዎች ተደግፋ ቀስ እያለች እያነከሰች የምትሄደው፡፡ በዚህ ምዕራፍ ሴት ልጅ እንደገና ራሷን የምትገነባበት ዕድል የምታገኝበት ሲሆን፤ በሌላ በኩል ደግሞ እንደ አለመታደል ሆኖ እውነትም ሁሉም ነገር በጉልበትና በኃይል መሆኑ አላስፈላጊ ክርን፣ ድቆሳ ይደርስባታል፡፡ አሁን አሁን ያ የትግል ሕይወት ቀርቶ ሁሉም ነገር በፍቅርና በስምምነት መሆኑ በሴት ልጅ ላይ ሊደርስ የሚችል አደጋንም ጭምር አስርቷል፡፡

· Tanaw ‘Filla’ ‹‹ፊላ ጨዋታ››

‘Filla’ ‹‹ፊላ›› ከቀርከሃ ወይም ከሸምበቆ የሚሠራ ባለብዙ ‘Fiilet’ ‹‹ፊለት›› ባህላዊ የትንፋሽ የሙዝቃ መሣሪያ ነው፡፡ ባህላዊ ጨዋታውም የ‹‹ፊላ›› ጨዋታ ይባላል፡፡ እያንዳንዱ የ‹‹ፊላ›› ‹‹ፊለት›› እንደ ‹‹ማይራ›› ከቀኝ ወደ ግራ በቁመትም ሆነ በውፍረት (ካንድ ቀርከሃ የሚቆረጡ ስለሆነ የውፍረት ልዩነት ተፈጥሯዊ ነው) የሚቀንስ ሆኖ፤ ሁለቱ የመጀመሪያዎቹ (‘Tontolit/Kasanit’, ‘Ensharit,) ከሌሎቹ ትንሽ በተለየ ሁኔታ የመርዘም አዝማሚያ ይኖራቸዋል፡፡ የመጨረሻዎቹ የተወሰኑት ትንንሽ ‹‹ፊለት›› ‘Fitinfitaya’ ይባላሉ፡፡ ሰፋ ሰፋ ያለ ቀዳደ አፍ ያለቸው ላይ እንደ ‹‹ማይራ›› ከቀርከሃው በጣም በአጭር አጭር የተቆረጠው አንድ ወይም ሁለት አፍ ‘Thoota’ ይገባለታል፡፡

‘Filla’ ‹‹ፊላ›› በርከት ያለ ‹‹ፊለት›› (30-40 ቀሰም) ይይዛል፡፡ በጨዋታ ጊዜ ከትልቁ (‘Tontolit/Kasanit’) መንፋት ይጀመርና ቀጣዩ የመጀመሪያው ሰው ነፍቶ እንደጨረሰ ይነፋል፡፡ በእንዲህ ሁኔታ በቅብብሎሽ እየነፉ እስከ መጨረሻው ይከዳል፡፡ ‹‹ፊላ›› የሚሰጠው የተለየ ወቅተልክ (Rhythm) ከ‹‹ሎላት››፣ እልልታ፣ እና በሥርዓትና ጥበብ በሚደረግ ውዝዋዜ ጋር ተዳምሮ እጅግ መሳጭ ባህላዊ ጨዋታ ነው፡፡ ምናልባት ሴቶች በቁጥር የማነስ ካልሆነ በስተቀር የፆታ ልዩነት የማይደረግበት ጨዋታ መሆኑ ደግሞ የበለጠ ሳቢና ማራኪ ያደርገዋል፡፡

‘Filla’ በበዓላት ጊዜ፣ በሠርግ ጊዜ እንዲሁም ‹‹ካላ›› የሰበሰቡትን ገንዘብ በሚበሉበት ጊዜ የተደረጁ ወጣቶች ወይም ሳይደራጁም ወጣቶች ተሰብስቦ ሲጀምሩ ሰዎች ዙሪያቸው ላይ ተሰብስበው የዚህ ገራሚ ባህላዊ ጨዋታ ይካፈላሉ፡፡ በበዓላት ጊዜ የተሰበሰቡትን ሰዎች የባህል ጨዋታ ወደሚካሄድበት መስክ እያደረሰ መንደር ለመንደር እየዞረ ሰዎችን ያሰባስባል፡፡

‘Targa’//Targa Technolgy//

አንድ ማህበረሰብ የሕይወት መስተጋብሩ እያደገ የሚሄድ፤ ከሚኖርበት የሕይወት ዘይቤ ወደሚቀጥለው ዘመናዊት የአኗኗር ስልት ሲሸጋገርና ሲያሸጋግር ይኖራል፡፡ ከአዳኝ-ሰብሳብነት ወደ አምራችነት ብሎም ወደ ዘመናዊ ቴክኖሎጂ ይሸጋገራል፡፡

የዺራሼ ማህበረሰብም እንደ ማንኛውም ማህበረሰብ ከአዳኝ-ሰብሳብነት ወደ አምራች-አርቢነት ሲሸጋገር ለአካባቢ ምቹ የሚሆን ምናልባትም ዘመን ተሸጋሪ ቴክኖሎጂ አብሮ በማሰብና በመተግበር ግንባር ቀደም በመሆን ‘Targa/Targa Technolgy/’ የ‹‹ታርጋ ወይም ታርጋ ቴክኖሎጂ›› ይጠቀማል፡፡ ‹‹ታርጋ›› ወይም ‹‹ታርጋ ቴክኖሎጂ›› የሰው ልጅ የተፈጥሮ ሀብቱ የሆነችውን መሬት ሲጠቀም ለወደፊት የማሰብ እምቅ አቅም እና ክህሎት ያሳየበት፤ ከአፈርና ውሃ ጥበቃ አልፎ ዝናብንና የዝናብ እጥረት ባለበት የሰው ልጅ እንዴት ምርት ማግኘት እንደሚችል የሚረዳ የአስተራረስ ስልት ነው፡፡ ‹‹ታርጋ›› ዘመን ተሸጋሪ እሳቤ በመሆኑ ቴክኖሎጂው ለሌሎች ማህበረሰብ ቢሸጋገር ጠቀሜታው በብዙ ዘዌ የጎላ ይሆናል፡፡

በማህበረሰቡ ዘንድ አንድ ወንድ (ሙሉ በሙሉ ሊባል በሚቻል ደረጃ) በራሱ ፍላጎትና ተነሳሽነት ራስ ወዳድነት በሌለበት አኳኃን ለመተዳደሪያው የምትሆን መሬት ይይዛል፡፡ ‘Heel’ ወይም የወሰን ድንበር (ድፍን ድንበር ወይም ለሁለት የተከፈለ ‘Kasiyal’) ከዙሪያ ጎረበት ጋራ ያካልልና መሬቱን ማረስ ሲጀምር ሙሉ እርሻውን በ‘Afaa’ ‹‹አፋ›› ይከፋፍላል፡፡ ‹‹አፋ›› ለመልከ ዓምድር ቆለቆል (Slopy) ፓራለል የሚሄድ በአማካይ 15 ሜትር ስፋት ይዞ የእርሻው ርዝመት ልክ ያለው ነው፡፡ የ‹‹አፋ›› ግማሽ ‘Mint Afaa’ ‹‹ሚንት አፋ›› ይባላል፡፡ ‹‹አፋ‹‹ በስራ ወቅት ስራን ለማቀላጠፍ እንዲረዳ ተደርጎ የተበጀ ሆኖ በአግድሞሽ የሚሄድ ጠበብ ባሉ ‘Targa’ ‹‹ታርጋ›› የተከፋፈለ ነው፡፡

‘Targa’ በ‹‹አፋ›› ስፋት ልክ በሚረዝሙ በሁለት አግድሞሽ (‘Moon/plural = Moonna’/) መካከል ከአንድ እስከ አንድ ተኩል ሜትር ስፋት ያለው ነው፡፡ ‹‹ታርጋ›› ወይም ‹‹ታርጋ ቴክኖሎጂ›› ዝናብ በሚዘንብበት ጊዜ ውሃው እንዳይወጣ ከትሮ ወይም ገድቦ የሚያስቀርበት ‘Pootaya’ ‹‹ፖታያ›› በውስጡ አለው፡፡ ‹‹ታርጋ›› በሁለት ወይም ሦስት ‘Kossoma’ ‹‹ኮሶማ›› ተከፋፍሎ ውሃ ማቆሪያ ገበታ በሚመስል ‘Pootaya’ የተሸነሸነ ነው፡፡

ማንኛውም ሥራ ሲሰራ እያንዳንዱን ‹‹ታርጋ›› ተከትሎ ስለሚሰራ አረም ሲታረም፣ አዝርእት ሲተከል፣ ጤፍ ሲዘራ፣ አጨዳ ጊዜ፣ አገዳ ነቀላ ጊዜ፣ ወዘተርፈ ጊዜ ውሃን ከመገደብ በተጨማሪ ሥራን ለማቀላጠፍ እጅግ ከፍተኛ ጠቀሜታ አለው፡፡ ‹‹ታርጋ›› ሦስት ወይም አራት ‹‹ፖታያ›› በውስጡ ሲይዝ፤ ‹‹ፖታያ›› ውሃ ታግዶ (Contained) የሚተኛበት የመሬት ጎርጓዳ መኝታ ነው፡፡

ማህበረሰቡ የዚሁ ‹‹ታርጋ›› ቴክኖሎጂ ሲጠቀም፤ አፈር ተፍጥሯዊ ለምነቱን በቀላሉ ሳይለቅ ለረጅም ዓመታት ምናልባትም ለክፍለ ዘመን እንዲቆይ በማድረግ አልፎም የዝናብ ውሃን ብቻ በመመርኮዝ መምረት መቻሉ እና ይህንን ትውልድ ተሻጋሪ የሆነ የአስተራረስ ዘዴንና አስተሳሰብ ለትውልድ ትሩፋት እያወረሰ ይገኛል፡፡ ‹‹ታርጋ›› እሳቤውና አተገባበሩ ተፈጥሮ የሰጠችውን ፀጋ ኃላፊነትና ተጠያቂነት በተሞላበት አግባብ በመጠቀም ለሰው ልጅ ጤንነት ተስማሚና ምቹ ምግብ የሆነው ከምውት አፈር (From organic soil) ማምረት ነው፡፡



ዺራሼ ባህል ዝምድና እና የተዛምዶ ዓይነቶች

አንድ ማህበረሰብ ከሚታወቅባቸው ነገሮች አንዱ ዝምድና እና የተዛምዶ ዓይነት ነው፡፡ ዝምድናና የተዛምዶ ሁኔታ እንደየማህበረሰቡ በጥቂቱም ሆነ በስፋት የሚለያይ፣ በማህበራዊ መስተጋብር ግንኙነት ውስጥ የክልከላም ሆነ ቅቡልነት ሁናቴ የሚወስን፣ ከሌላው አጎራባች ማህበረሰብ ጋር ስላለው የህልውና ትስስር ማመላከቻ፣ እንዲሁም የማህበረሰቡ ወግና ሥርዓት አካል አድርጎ የመስተዳድር ሂደትን ጤንነት መጠበቂያም ነው፡፡ የዝምድናና ተዛምዶ እሳቤ እንደየማህበረሰቡ እይታ የሚወሰድ፣ ሁሉም ማህበረሰብ በራሱ እይታ ትክክል፣ ፍጹም የኾነ የተዛምዶ ዓይነት ይህ ነው ተብሎ ማስቀመጥ የማይቻል፣ አንዱ የአንዱን እሳቤ ማክበር፣ ማስከበር፣ መቀበል፣ መቀባበል ያለበት ጉዳይ ነው፡፡

የዺራሼ ህብረተሰብም የሚታወቅበት የራሱ የሆነ የዝምድናና ተዛምዶ ግንኙነት አላቸው፡፡ ማህበረሰቡ በ“Eg’e” ወይም ጎሣ አስተዳደር ሥርዓት የሚመሩ፣ በጋብቻ ትስስርም ሆነ በሌሎች ተዛምዳዊ ግንኙነት ውስጥ የራሳቸው የሆነ የዝምድና ዓይነት ያላቸው፤ በዚህ እሳቤ ውስጥ ማህበረሰቡ በሙሉ የሚተዳደርበት የትውልድ ወግና ሥርዓት ነው፡፡

በዚህ መሠረት አንድ ሰው ከዘጠኙ ጎሣዎች መካከል የአንድ ጎሣ ቤተሰብ መሆን የውዴታ ግዴታው ሲሆን፤ የጎሣዉ ቤተሰብ በሙሉ የዘር ወይም የትውልድ ግንኙነት ይኖራቸዋል፡፡ በጎሣው ውስጥ የዕድሜ እኩዮቹ ወንድም/እህት (Alaw/Alawt)፣ ታላላቆቹ ታላቅ ወንድም/እህት (Angas/Angashet)፣ ታናናሾቹ ታናሽ ወንድም/እህት (Enshar/Eshart)፣ ያባቱ/የናቱ እኩዮቹ አባት/አክስት (Apaa/Mamot)፣ የልጆቹ እኩዮቹ ልጅ (Em/Enant) ይሆናል ማለት ነው፡፡ የገዛ አባት ወንድምና እህት አባት/አክስት (Apaa/Mamot) ይሆናሉ ማለት ነው፡፡ ስለሆነም ከጎሣዉ ቤተሰብ ጋር መጋባት፣ ግብረ ሥጋ ግንኙነት ማሰብ፣ መፈጸም በፍጹም ነውር ነው፡፡

ሁለተኛው የዝምድና ዓይነት በጋብቻ ትስስር ውስጥ ነው፡፡ ይህም አንድ ሰው የገዛ ወላጅ አባት/እናት ይኖረዋል፡፡ ምናልባት አባቱ ሁለት ወይም ከዚያ በላይ ሚስቶች አግብቶ እንደሆነ ሌላ እናት ‹‹የእንጀራ እናት›› ይኖረዋል፡፡ በእናት በኩልም ተመሳሳይ ነው፡፡ እዚሁ ጋ የእናት እህቶች በሙሉ እናት ናቸው በባህሉ ወግ መሠረት፡፡ የናት ወንድሞች ደግሞ ‘Abb’/አጎት ይሆናል ማለት ነው፡፡ የእናት እህቶች ባሎች በሙሉ አባት ሲሆኑ፤ የወንድሞቿ ሚስቶች ደግሞ ‘Abunt’ ይሆናሉ ማለት ነው፡፡ የሚስት አባትና እናት ለባል አባትና እናት ሲሆኑ፤ የባል አባትና እናት ለሚስት በቅደም ተከተል አማት/‘Haaqa’ እና አማት‘Haqitot’ ይሆናሉ፡፡ የልጅ ሚስት ምራት/‘Haybat’ ስትባል፣ የልጅ ባል ደግሞ ልጅ ይባላል፡፡

የእህት ባል ለወንድሟ ‘Tarmash’ ወንድሟ ለባሏ ‘Soda’ ሲሆን፤ እሱ ለእህቶቿ ‘Angas/Enshar’ (ታላቅ/ታናሽ ወንድም እንደ ማለት ነው) እህቶቿ ለሱ ‘Angashet/Eshart’ (ታላቅ/ታናሽ እህት እንደ ማለት ነው) ይሆናል፡፡ የእህት ልጅ ለወንድሞቿ ‘Ashim’ (ወንድ) ወይም ‘Ashint’ (ሴት) ይሆናሉ፡፡ የወንድም ሚስት ‘Angashet/Eshart’ ወይም እሷ ለእህቶቹ ‘Awlat’ ይሆናል፡፡ ያባት/የእናት አባት/እናት ወንድ አያት ‘Ahhaya’ ሴት አያት ‘Ahoot’፣ … እያለ እስከ ‘Ashu’ ወደኋላ ይቆጠራል፡፡ የልጅ-ልጅ ወንድ/ሴት Obob/Oboft ሲባል፤ የልጅ-ልጅ ልጅ ‘Oppa’ ይሆናሉ፡፡

በህብረተሰቡ ዘንድ ድርብ ጋብቻ የተለመደ ነው፡፡ የመጀመሪያዋ አሚን ሚስት ‘Kordhitot’ ስትባል፤ አልፎ አልፎ በእርሷ ፈቃድ አሊያም ባል በገዛ ፈቃዱ ብቻ ሁለተኛና ከዚያ በላይ ሚስት ‘Hillaot’ ሊያገባ ይችላል፡፡ የመጀመሪያዋ ሚስት ‘Kordhitot’ በባህሉ የጣውንቶቿ/ጎባኖቿ ዋና አስተዳዳሪ ትሆናልች፡፡ የውርስ ጋብቻም የተለመደ ነው፡፡ እነዚህ ጣውንታት ባብዛኛውን ጊዜ በሠላም ዝምድና ተዋድዶ አብሮ ይኖራሉ፡፡

ባጠቃላይ የአባት ወንድሞችና ዘመዶች አባት ሲሆኑ፤ ያባት እህቶችና የዘመድ ሴት ልጆች ኣክስት/‘Mamot’ ይሆናሉ፡፡ የእናት እህቶች እናት ሲሆኑ፤ የእናት ወንድሞች አጎት/‘Abb’ ይሆናሉ፡፡ ስለዚህ የእናት ሐረግ ወይም ጎሳ ባጠቃላይ ‘Abunt’ ተብሎ ይጠራል፡፡


Punita ne Shukeat//ቡና እና የቡና ቅጠል//Coffee Punit ‹‹ፑንት›› ወይም ቡና በዓለም አቀፍ እየበቀለ ያለው የአመጣጡ ታሪክ ሲፈተሽ ከጥንት ዝንታዓለም በኢትዮጵያ ኮረብታዎች ላይ ነው። በተለያየ አህጉራት እና የሚበቅል በብዙሃኑ ማህበረሰብ ዘንድ ተወዳጅ የሆነ ቡና ወይም በኪቶሊያ ‹‹ፑና›› በንግድ ምክንያት እንደተበተነ ይነገራል። ‹‹ፑንት›› አራት ዋና ዋና ዘር አለው፡ እነሱም አረብካ፣ ሮቡስታ፣ እክሰልሳ እና ሊበሪካ በመባል ይታወቃሉ። የኪቶላ ሕዝብ ‹‹ፑንት›› በማምረት ከሚታወቁ ማህበረሰቦች አንዱ ናቸው። አካባቢው ሦስት የአየር ጸባይ ስላለው በተለይ በደጋ እና በወይናደጋ በደንብ ያመርታሉ። ማህበረሰቡ ቡናን ለመድኃኒትነት፣ ለአነቃቅነት ሲጠቀሙ፤ ተረፈ ምርቱን ለገቢ ምንጭነትም ይጠቀማሉ። የቡና ፍሬ በሸክላ ጠቆር እስኪል ድረስ በደንብ ተቆልቶ፤ በጣም ሳይላም በሙቀጫ ወይም በቤት ወፍጮ ተሸርክቶ፤ በጀበና የተፈላው በባዶ ወይም በቅቤ ለጉንፋን፣ ለራስ ምታት፣ ወዘተ አሊያም ለማነቃቂያነቱ ይጠጣል። የደረቀው የቡና ቅጠል ‹‹ሹኬት›› ተሰብስቦ ከተለያዩ ቅመማ ቅመም (ድምብላል፣ በሶብላ፣ ነጭ ሽንኩርት፣ በርበሬ፣ ... ) ጋር በምጣድ ላይ አመስ አመስ ተደርጎ በሙቀጫ ወይም በደንብ እስኪልም ድረስ ይወቀጣል። ድቅቁን በዕቃ ተቀምጦ ጧት ጧት በፈላ ውሃ ተበጥብጦ ከምግብ ጋር ፉት ይደረጋል። ‹‹ሹኬት›› ተቀሜታው ብዙ ነው፤ የምግብ ፍላጎትን ይከፍታል፣ አነቃቂም ነው። በቅቤም ወይም በማንኛውም ባህላዊ መጠጥ ጋር ይጋታል። ያልደረቀ ቅጠል ከተለያየ ቅመማ ቅመም ጋር በሸክላ ድስት ሌሊቱን ሙሉ ተቀቅሎ ካደረው ሾርባው ‹‹ቶልጫ›› ተንጠፍጥፎ ይጥጣል።



Saga ne Qac maniya?

እንደ ዓለምም ሆነ እንደ አፍሪካ ለአንዳንድ ነገሮች ማህበረሰባዊ አተያይም ሆነ ትርጉም መስጠት የተለመደ ነው። በተለይ አፍሪካ አስማታዊ እምነቶችና ትርጉም የበዛባት፤ እስከ ዛሬ ድረስ በተለያየ ማህበረሰብ ውስጥ በተለያየ አለበለዚያ በተመሳሳይ አውደ እሳቤ በመነገር ላይ ይገኛሉ። ኢትዮጵያ ከእነዚህ ማህበረ ባህላዊ እሳቤዎችና እምነቶች የጸዳች አገር አይደለችም። ‘ኪቶላ’ ብሔረሰብም እንደ አንድ ማህበረሰብ የሚያምንባቸው ሁለት ባህላዊ እምነቶች ‘Sag’‹‹ሣግ›› እና ‘Qac’‹‹ቃጭ›› ናቸው።

‘Sag’ ወይም የ‹‹ሣግ›› አስተሳሰብ በጽንሰ ሀሳብ ደረጃ ከፍ ያለ ምልከታ ያለው፤ በዚህ ‹‹ሣግ›› የሚወለዱ ወይም እላያቸው ላይ የገባባቸው ሰዎች ከሌላው ማህበረሰብ ዘንድ የሚፈሩ፣ ክብር የሚሰጣቸው፣ የፈጣሪ ኃይል እንዳረፈባቸው ይቆጠራሉ። እንደሚባለው ይህ ኃይል አንድ ሰው ገና ሲወለድ ወይም አልፎ አልፎ ካደጉም በኋላ በላያቸው ሊያርፍ ይችላል። እንደ ማህበረሰቡ እምነት ከሆነ በእነዚህ ሰዎች ላይ ተዓምር የሚሰራው ኃይል ‹‹ሣግ›› እንደ አብሮሆተ እግዚአብሔር ስለሚታሰብ ሰዎችን እንደየደረጃቸው እና እንደየተግባራው ያከብራሉ።

ከንጉሥ ወይም ‘Dham’ ‹‹ዻም›› አንስቶ እስከ ታችኛው እርከን ያሉ እነዚህ አስማታዊ ኃይል የሚያርፍባቸው ሰዎች እንደተሰጣቸው መጠን እና ፈርጅ የየራሳቸው የሥራ ድርሻ አላቸው፡፡ ለምሳሌ ያክል በሽታን፣ ሰይጣንና ወፍን በማራቅ፣ በአካባቢው ሠላም እንዲሆን እንደሚያደርግ እና የአካባቢው ህብረተሰብ ሳይታዘዝላቸው ሲቀር ደግሞ በአካባቢው ላይ ከላይ የተጠቀሱ በሽታ፣ ሰይጣንና የደረሰ ነጭ ማሽላ(ራር) በመብላት የሚታወቅ ወፍ ወይም “ካይሎት” በመልቀቅ ህብረተሰቡን የሚያስደነግጥ ድርጊት የመፈፀም ታዓምራት በመስራት ህዝቡ ያንን በመፍራት ክብር እንድሰጡት በማድረግ በታሪክ ይታወቃል። አንዳንዶች ደግሞ ወንዝን በማድረቅ፣ የተሰነጣጠቀ መሬት እንዲገናኝ በማድረግ እና በአካባቢው አንድ ነገር ሲሰረቅ ሰዎች ከካይማለ ዘንድ በመሄድ ሌባው እንዲገደል ይለምናሉ፣ ካይማለም መብረቅና ነጎድጓድ በማውረድ ሌባውን በመግደል በአጠገቡ የሰረቀውን ዕቃ የመጣል ታዓምራት ያደርጋሉ። ሌሎች ህብረተሰቡ እንዲታዘዙላቸው በአስማት ኃይል ተኩላ፣ ጅብ፣ እና ነብር በህዝቡ ላይ የመልቀቅ መናፍታዊ ኃይል ይሠራሉ። ሌሎች እንደነ ‘sohayt’ ‹‹ሶሃይት›› እና ‘thootha’ ‹‹ጦ’ጣ›› ዕውቀትን የመግለጥ ኃይል ወይም ታዓምር ስለሚያደርጉ ሰዎች ወደ እነሱ ሂደው ስውር ምስጢራቸውን ያስገልጣሉ።

‘Koyma’ ‹‹ኮይማ››፣ ‘Hulul’ ‹‹ሁሉል›› እና ‘Orayt’ ‹‹ኦራይት›› እሳቤዎች በማህበረሰቡ ዘንድ ተቀባይነት የለላቸው እምነቶች ስለሆኑ ከእነዚህ በአንዱ የሚታማ ሰው ወይም ቤተሰብ ‹‹ቃጭ ቃባን›› ወይም ጽዩፍ ነው ተብሎ ይታመናል። አንድ ሰው የትዳር አጋሩን ምርጫ ከመወሰኑ በፊት ስለ እነዚህ በማህበረሰቡ ዘንድ ተቀባይነት ስላጡ ምድራዊ ማንነቶች ጠይቆ ማረጋገጥ ይኖርበታል። ስለዚህ በማህበረሰቡ ዘንድ ሁለት ስውራዊ ጎራዎች (ሐላ) አሉ፤ ጤነኛ ጎራ እና ጤነኛ ያልሆኑ ‹‹ቃጭ›› አለባቸው ተብሎ ይከፈላሉ።

‹‹ኮይማ›› የሚባለው በመመልከት ቀልቡ ያረፈበትን ሰው፤ እንስሳ፣ ወዘተ በዓይኑ የመውጋት ችሎታ ያለው ሰው ሲሆን፤ የተወጋው ቀስ በቀስ አንዳንዴ በቅጽበት ጉዳት የሚያስተናግድ ይሆናል። ‹‹ኦራይት›› የሚባለው ከኮይማ አደገኛ እና ከበድ ያለ ጉዳት የሚያደርሱ ተጋላጮች ጩኸት እያሰማ የበይውን ስም እየጠራ ይወተውታል። የዚህ ዓይነቱ ማንነት ከኪቶላ ሕዝብ ዘንድ እምብዛም የሚስተዋል ባይሆንም ግን ከመጤ ማህበረሰብ ጋር ተያይዞ የመጣ እንደሆነ ይታመናል። ‹‹ሁሉል›› የሚባለው ማንነት ከእነዚህ ከሁለቱ ማንነቶች የተለየ ሦስተኛ ወገን ላይ ጉዳት የለለው ግን የዚህ የምድራዊ ማንነት ሰለባ የሆነ ሰው ከሞተ ሬሳው ከልክ በላይ የሚነፋ ነው። እንደ አፈ ታሪክ ትርክት ከሆነ ይህ ችግር ጥንት ያልነበረ ግን በአንድ ወቅት ከባድ ድርቅ በአካባቢው ላይ ተከስቶ የሚላስ የሚቀመስ ጠፍቶ ሰዎች ያገኙት ሲበሉ ነበርና በዚህን ጊዜ አዋልድጌሳ የበሉ ሰዎች የዚሁ ‹‹ሁሉል›› ሰለባ እንደሆኑ ይወጋል።

እንደ ማህበረሰቡ እምነት ከሆነ እነዚህ ማንነቶች የሚተላለፉት በጋብቻ (ከባል ወደ ሚስት እና በተለዋጪ) እና በዘር እንዲሁም ‹‹ኦራይት›› ወዶና ፈቅዶ በእንዲህ ዓይነት ሥራ ውስጥ በመግባት ነው። ሌላው አስገራሚ ነገር የሁሉል ማንነት ሰለባ የሆነ ሰው ለሞት በሚያጣጥር ላይ ካለው ጋር በትንፋሽ ከተገናኘ የዚሁ የሰላም ሰውም ሬሳም ይነፋል ይባላል። ሁሉም በወንጌል በማመን ብቻ የሚወገዱ ማንነቶች ናቸው።

31 views0 comments
Post: Blog2_Post
bottom of page