top of page

ትግል/Struggle

Updated: Apr 17

ትግል ምንድን ነው? ትግል በመደብ ስም ሲሆን (1) አንዱ ሌላውን ለመጣል ወይም ለማጥቃት፣ ... ወዘተ የሚያደርገው ትንቅንቅ፣ ፍትጊያ፣ ግብግብ፤ (2) ተግባርን፣ ሥራን ለማከናወን የሚደረግ ጥረት፣ መፍጨርጨር፤ (3) ብዙውን ጊዜ የፖለቲካ ዓላማን ለማሳካት የሚደረግ ጥረት፣ መፍጨርጨር የሚሉ ትርጉሞችን ይይዛል። በዚህ ጽሑፍ ውስጥ ትግል የሚለው ጽንሰ ሐሳብ የሁለተኛ እና የሦስተኛ ትርጉሞችን ብቻ ያትታል።  

በዺራሼ ማህበረሰብ ዘንድ “Kallat errot” ይላሉ አበው የሚል በጣም የተለመደ አባባል አለ። ትርጓሜው ኑሮ ትግል ወይም ኑሮ በጥረት ነው የሚል ይሆናል። የወንዱ ዘር እና የሴቷ ዕንቁላል ጥምረት ፈጥሮ ለመኖር የወንዱ ዘር ከተረጨበት ከሴቷ ክፍል ዕንቁላል ያለበት ቦታ ለመድረስ ከፍተኛ የጉዞ ትግል ማድረግ አለበት። ዕንቁላሉ ጋ ደርሶ እንኳ ውህደት ለማድረግ ዕንቁላሉን ለመስበር ከፍተኛ ጥረት፣ ትንቅንቅ ማድረግ ይጠበቅበታል። የተዋሄደው ውህድ ደግሞ ሽቅብ ወርዶ በማህጸን ግድግዳ ላይ መተከል፤ ዘጠኝ ወራት የሚቆይበት ሁናቴ፤ ዘጠኙ ወራት እንዳለቁ መዘቅዘቅ፤ ማህጸን ከፍቶ ለመውጣት የሚደረገው ትንቅንቅ፤ አዲስ ከባቢ ጋር ለመላመድ የሚደረገው ትግል፤ ... ወዘተ እያለ እስከ ዕለተ ሞት ድረስ ባለው በሕይወት ምዕራፎች ያለው የትግል መዓት እና ዓይነት አቤት ከቃላት ያልፋል።

ሌላው ቀርቶ ሰው የተገኘበት ፈጣሪ አምላኩን ለማምለክ እንኳ ከዓለም፣ ከሥጋ እና ከሰይጣን ጋር ዘመኑን ሁሉ ይታገላል። ሐሳቡንና ፈቃዱን በፈጣሪው ሥር ለማስገዛት የሚደረገው ትግል ወደር የለውም። በአካለ ሐሳብ መዋቅር በሆነችው ዓለም ውስጥ የሚያሳስቱ፣ የሚያደናቀፉና ቀርንፎ የሚያስሩ ነገሮች ቁጥር ስፍር የላቸውም። የስህተት መንገዶች ብዙውን ጊዜ አስተማሪ የላቸውም፤ በተቃራኒው ትክክለኛንና የመልካም መንገዶችን ለማስተማር በርካታ አስተማሪዎች ይጥራሉ፣ ይለፋሉ ብቁነቱ ግን የተለፋው ያክል አይደልም። ለምሳሌ አንድ አዳጊ ልጅ ፊት ነጠላ ጫማ አስተካክላችሁ ጫማውን አስር ጊዜ በራሱ እንዲያደርግ  ብታደርጉት የግራውን በቀኝ፤ የቀኙን በግራ እግር ሥር የማድረግ እድሉ ሰባ አምስት በመቶ ይሆናል። ይህ ማለት በክንውንም ሆነ በሐሳብ ነጓጆች በአብዛኛው በተሳሳተ መንገድ ላይ ሊሆኑ ስለሚችሉ፤ እነዚህ ወደ ትክክለኛው መንገድ ለመመለስ ከፍተኛ ትግል  ይጠበቅባቸዋል።         

የሰው ልጅ ሕይወት በራሷ ሁሉም በሙላት በተሰጠበት ነጻነት ከሞላበት ከባቢ በአዳም ውድቀት ምክንያት ከወጣች ወዲህ በእሾህ እና በአሜከላ ከበባ ውስጥ ማለትም በውስብስብ ችግሮች ተከብባ፤ በእነዚህ ውጥንቅጦች ውስጥ ሆና በከፍተኛ ድካም ዘመኗን ሁሉ ትፍጨረጨራለች። የሰው ልጅም ያ ያኔ የነበረበት  ሀሳባዊት ከሆነችው ከዔድን ገነት ያጣውን ምቾት እና መደላደል በአሁኗ ምድር ላይ ለማግኘት ሀሳቦችን ደምሮና ቀንሶ፣ አባዝቶና አካፍሎ፣ አውጥቶና አውርዶ፣ አግባብቶና አሰናስኖ በጥረት እና በግረት ለዝንታዓለም ዘመናት ይታገላል።

ምድር ከነጻ ሰጭነት ፍጹማዊ ሙላት ሀብቶቿ ወደ ተደበቀባት ሥነ ሥርዓት ከተቀየረበት ጊዜ አንስቶ የሰው ልጅ ጉድለቷን ለመሙላት ከፍተኛ ጥረትና ግረት በተሞላበት ሁኔታ ሲኳትን ይኖራል። እነዚህ ለሥረ ዕድገት መሠረት የሆኑት የተፈጥሮ ሀብቶች ዓይነትም ሆነ የተሰራጩበት ሁኔታ ለመለየት በራሱ ልዩ የሰው ልጆች የትብብር ትግል ይጠይቃል። በሌላ በኩል ዕድገትን ለመጀመርም ሆነ ሥረ መሠረቱን ለማጽናት አጋዥ የሆነውም ቴክኖሎጂ ለመፍጠርም ሆነ ለማላመድ የምጡቅ ስብስብ ጭቅላቶች ከፍተኛ ትግል ያሻል።

ዓለም በብዙ ሥርዓታት ተሳስራ፤ በርካታ ፍጡራንን ደግሞ በሥርዓቷ ያስተሳሰረች ‘‘የአካለ ሀሳብ’’ ውቅርት ናት። ዓለም በውስጧ ሁለት ትልልቅ እርስ በርስ የተከረነቱ የአካለ ሀሳብ መዋቅሮችን የያዘች ናት። አንደኛው ሕይወት ያላቸው ሰውን ጨምሮ የሚኖርበት ምድር፣ መሬት፣ ክፍለ ዓለም ስትሆን ሌላኛው ሥርዓትና ስሜት የሚዋኙበት ክፍለ ረቂቅ (Abstract world) ናት። የዓለም አካለ ሀሳብ አወቃቀር ሲታይ በተለምዶ ያደጉ እና በማደግ ላይ ያሉ ሀገራት ተብሎ ሲጠራ በተለየ ሁኔታ “ከዕድገት በታች ያደጉ ሀገራት” ተብሎ የሚዘረዘሩ እንዳሉ ከግንዛቤያችን አልጠፋም።

ሁሉም ሀገራት በለውጥ እና በዕድገት ምዕራፎች አልፎ ካደጉት ተርታ መመደባቸው አይቀረ ጉዳይ መሆኑ ቢታመንም የሀሳብ፣ የጊዜ፣ እና የቦታ አጠቃቀም ሁኔታን ሊያፈጥን ወይም ሊያዘግይ ይችላል። ሀሳባቸውን፣ ጉልበታቸውንና ዕውቀታቸውን ሰብሰብ አድርጎ እምቅ አቅማቸውን በጊዜ አውቆ በትክክለኛ ቦታ ላይ ያዋሉት ሀገራት በኢኮኖሚውም ሆነ በእሳቤ ልቀት አድገዋል፤ እያደጉም ይገኛሉ።

በታሪክ ቅብብሎሽ ውስጥ ከታሪክ መዛግብት ትንተና ወይም ከህያው ምስክሮች  የምንገነዘበው የሰው ልጅ በትግሉ ያስመዘገበው የዕድገት ውጤቶች ይለያያል። ትግሎች እንደ ዘመኑ ሁኔታ፣ ሥልጣኔ፣ ሰዎች የደረሱበት መረዳት እንደሚለያዩ ሁሉ ዓላማቸው፣ ይዘታቸው፣ ስልታቸውና አውዳቸው ይለያያል። የብዙ ትግሎች ዓላማ ለመገንባት፣ ለለውጥ፣ ለዕድገት፣ ወዘተርፈ ሲሆን፤ ለማፍረስ፣ ለማደናቀፍ፣ ለመጣል፣ ሌሎች ላይ በኃይል ለመጫን፣ ወዘተርፈ የሚደረጉም ትግሎች ጥቂቶች ኣይደሉም።   

ትግል የአንድ አካባቢ፣ የክፍለ ሀገር፣ የሀገር፣ ወይም የሀገራት ጥምረት ይዘት ኖሮት የፖለቲካ፣ የኢኮኖሚና የማህበረሰባዊ እንደምታን አንግቦ ሰዎች በተለያዩ መታገያ ስልቶች ሊተባበሩ ይችላሉ። የሀገራችን ኢትዮጵያም ሆነ የአካባቢያችን ጋርዱላ ዞን የሚታዩ የትግል አውዶች ከእነዚህ የተለየ አይደሉም። እንደ አንድ ሀገር ዜጋ ከአካባቢዉ ማህበረሰብ በተለይም ደግሞ ምጡቅ ምሁራንና መሪዎች ጋር “በድር ቢያብር አንበሳ ያስር” ሁኔታ መያያዝ፣ መተባበር፣ መደማመጥ፣ መረዳዳት ለአዎንታዊ ውጤት የጎላ አስተዋጽኦ ስለሚኖረው በሕብረ ብሄራዊነትና በወንድማማችነት እሳቤና ተግባር ማዕቀፍ ውስጥ መሆን የውደታ ብቻ ሳይሆን የግዴታም ጭምር ይሆናል።   

ታዲያ ትልማችንን ለመገንባት፣ ለለውጥ፣ ለዕድገት እና ለልማት መሆን ካለበት ሀገርንና ፖለቲካን፣ ዛሬና ነገን፣ መንገድና ሜዳን፣ ስልትና ሥርዓትን በአግባቡ አጥርቶ መለየት ተገቢ ይሆናል። ብዙዎቻችን ትናንትና ስንጫወትበት የነበረው ኳሱና ሜዳው ለነገዋ ኢትዮጵያ ገጽታ ግንባታ በሚሆን መልኩ ሳይሆን መንግሥትንም ሆነ ማህበረሰብን በማጥላላት፣ በማንቋሸሽ፣ አልፎም በመሳደብ እንዲሁም የተሠራውን ከልክ በላይ በማንኳሰስ፤ ጉድለቶችን ከልክ በላይ ለጥጦ በማግነን የሁለት ወይም ከዚያም በላይ ሀገራት ሰዎች ሆነን ነበር።  

እንዲህ ዓይነት የእኛ እና የእነርሱ ተረክ የጋራ የሆነ ታላቅ ትርክት አሳጥቶናል፤ እያሳጣንም ይገኛል። የትናንትና ታሪካችን እንደሚያስረዳን በፖለቲካውም ሆነ በኢኮኖሚውም አንድ የጋራ ማህበረሰብ መገንባት ላይ ሰፊ ክፍተት እንዳለብን፤ ሀገርን እንመራለን ብሎ የሚደራጁት ፓርቲዎች ሁሉ ከስም ስያሜዎቻቸው ጀምሮ እስከ ተግባሮቻቸውም ጭምር አግላይ፣ አሳታፊነትና አካታችነት የሌላቸው ነበሩ፤ አሁንም አሉም።   

በሌሎች ሀገራት ከአፍሪካ ሀገራት ውጭ ሀገር እና ዓላማ ዕንቁ የጋራ ፈርጦቻቸው ናቸው። ስለዚህ የሚደረገው ማንኛውም ትግል በሐሳብ ልዕልና ወይም በመታገያ ስልት ላይ ይሆናል ማለት ነው። የተሻለ ሐሳብ በተመረጠ የመፈጸሚያ ስልት ወይም ሥነ-ዘዴ (Methodology) የተቀመርው ገዢ ይሆናል። የፖለቲካ ተፎካካሪ ፓርቲዎች መመሥረቻ መነሻ ሐሳባቸውም በእነዚህ በሁለቱ ጽንሰ ሐሳቦች ላይ ያጠነጠነ ይሆናል ማለት ነው።

በአፍሪካም ሆነ በኢትዮጵያ የትግል ጽንሰ ሐሳብ በዋናነት “አንዱ ሌላውን ለመጣል ወይም ለማጥቃት፣ ለማሸነፍ፣ ለመጉዳት፣ ... ወዘተ የሚያደርገው ትንቅንቅ፣ ፍትጊያ፣ ግብግብ” ላይ ያረፈ ይመስላል። እንዲህ ከሆነ የጋራ ሀገር እና ዓላማ ልኖረን አይችልም ማለት ነው። የሠፈር ነጻ አውጪ፣ የቀጠና ነጻ አውጪ፣ ወዘተርፈ ሆነን ከገምስ በላይ ጠላት በሀገር አፍርተን፤ የነጻ አውጪ ታጋይ ግን ነጻነት ናፋጊ፤ በነገ ነጻ አውጪዎች ተወጋጅ፤ በተራው ቀጣይ ለነጻነት ታጋይ፤ እንዲህና እንዲያ የእምቡሽዬ አዙሪት ውስጥ መዳከር ነው ፍሬ ነገሩ። ለነገ የማይባል የቤት ሥራችን የሚሆነው ከእንዲህ ዓይነት ትግል ወጥተን “በሐሳብ የበላይነት ወደምንጫወትበት ሜዳ” ላይ መሰለፍ ግዴታችን ነው።  

18 views0 comments

Recent Posts

See All

Geology and Geologic Resources of Ethiopia (Geol 502)

Course outline Chapter -1 African Geology Chapter-2 Geology and Structure of the Ethiopian Basement Chapter-3 Phanerozoic Sedimentation History of the Horn of Africa Chapter -4 Cenozoic Magmatism in t

Volcanology and Geothermal Resources (Geol 4132)

Course outline References Chapter -1 Application of Volcanological Observations to Geothermal Exploration Chapter-2 Recent Practical Advances in Volcanology Chapter-3 Pyroclastic Rocks as a Tool to Ev

Post: Blog2_Post
bottom of page